ጥናት (አጠናን) ሲባል በቃል መያዝን ብቻ ሣይሆን በተግባር ማሣየትንም ያካትታል።
ዘለዓለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል በጥሩ አነሳስ ወይም አጀማመር የሰው ልጅ በቃልና በኑሮው እንዲሁም በተግባር እያጠናው እንዲጠቀምበትና እንዲጠቅምበት የአጠናኑን መክፈቻ ቁልፍ መስጠት ወይም በሩን ማሣየት ነው።
ኢያ 1፥8፣ ዘዳ 6፥6፣ ኤፌ 6፥7፣ ሮሜ 15፥4፣ ጢሞ 3፥16-17
መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ሐረግ መጽሐፍና ቅዱስ በሚሉት ሁለት ቃላት ጥምረት የተመሠረተ ሲሆን ሁለቱ ቃላት ከተለያዩ የንግግር ክፍሎች የተወጣጡ ናቸው። መጽሐፍ የሚለው ስም ሲሆን ቅዱስ ቅጽል ይባላል። የቃላት ህብረት ሐረግን ሊመሠርት በመቻሉ ሁለቱ ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን አንድ ሐረግ ሊመሰርት ችሏል። ይህ ሐረግ የአንድ መጽሐፍ ርእስ ለመሆን እያገለገለ ይገኛል። መጽሐፍ ጸሐፈ ጻፈ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ዮሐ 19፥19፣ ኢሣ 10፥19
መጽሐፍ፥ ስንል ደግሞ በአንድ ጥራዝ ስር ተጠቃሎ የተሰበሰበ ጽሑፍ
ቅዱስ፥ ቀደሰ አመሰገነ፣ አከበረ፣ መረጠ፣ ለየ፣ አነጻ ማለት ነው።
ቅዱስ ሲል፥ ደግሞ ልዩ፣ ክቡር፣ ምስጉን፣ ንጹሕ፣ ምርጥ ማለት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ፥
ስያሜው፥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ርእስ የተሰጠበት ጊዜ ተወስኖ ባይታወቅም ባይነገርም አስቀድሞ ምን ይባል እንደነበርና ቅዱስ የሚለው ቅጽል ሊጨመርበት ያስፈለገበትን ምክንያት እንዲሁም በሌሎች ቋንቋዎች ይህ ርእስ ሲጠራ ምን እንደሚመስል እንመለከታለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎች አሻሚ መጻሕፍት ባልነበሩበት ወቅት መጽሐፍ ብቻ ተብሎ ያለ ቅጽሉ እየተጠራ እንደነበር በራሱ በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት ጥቅሶች አስረጅዎች ናቸው። ኢሣ 34፥16፣ 1ኛ ቆሮ 15፥4። በሌሎች የመጽሐፉ ክፍሎች ደግሞ እስከ ቅጽሉ ሲጠራ እንመለከታለን። ሮሜ 1፥2። በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ መጽሐፍ ወይም መጻሕፍት ሲል የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ማለቱ ነው። ዮሐ 7፥38
መጽሐፉ ቅዱስ ሊያስብሉት የሚችሉ ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተሉት ይገለጻሉ። መጽሐፉ ቅዱስ ነው ምክንያቱም
መጽሐፉ የደረሳቸው ሰዎች ሁሉ እንደየቋንቋቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ርዕስ ለመስጠት
ሞክረዋል። ለምሣሌ
ኒቅያ በምትባል ሐገር ቢብሎስ የምትባል አነስተኛ ከተማ ነበረች ። ከዚህችም ከተማ ግሪኮች ፓፒረስ የተባለውን በዚያን ጊዜ ለጽህፈት ያገለግል የነበረውን መጻፊያ ከዚያ ያስመጡ ስለነበረ፣ ስሙን ቢብሎስ (ነጠላ) ቢብሊያ (ብዙ) በማለት የማንኛውም መጽሐፍ ስም አድርገውት ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ታላቅ ፍጥረተ ዓለም አስገኝ የሆነውን እግዚአብሔርን በክብርና በግርማ በብዙ ሞገስና የሀጢአትን ቅጣት በሚሰጥ ፃድቅነት ይገልፀዋል። (ዘፀ 34፥6-7)
የመጽሐፍ ቅዱስ 2ኛው ታላቅ ክፍል አዲስ ኪዳን ደግሞ እግዚአብሔርን በፍቅሩ በርህራሄውና በቅርብ አባትነቱ ይገልፀዋል። (ማቴ 6፥9፣ ዮሐ 1፥18፣ ሮሜ 8፥15)።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ታሪክ፣ ስለ ሳይንስ፣ ስለፍልስፍና እና ስለ መልክዓ ምድር የሚናገር መጽሐፍ ቢሆንም የሳይንስ ወይም የጂኦግራፊ መጽሐፍ ግን አይደለም። ሰዎች ከቆሙበት አላማና ሙያ አንፃር የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ቢጠቅሱትና አጋር ቢያደርጉትም የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ አላማ ግን ድህነተ ነፍስ የተፈጸመበትን ቤዛ ኩሉ ዓለም ክርስቶስን መስበክ ነው። ለዚህ ነው የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ዮሐ 3፥16ን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅል ሐሣብ የሚሉት ።
መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት በቅንነት የሚተጉ ወገኖች አያሌ ናቸው። ይህ አጭር ጥናትም እነዚህን ወገኖች ለመርዳት የታሰበ ነው። ለብዙ ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስን የመረመሩ ሰዎች እንደሚናገሩት መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም መዝገበ ቃላት፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ ስፍረ ዘመንና መልከዐ ምድራዊ ጥናቶች ወሳኝ ቢሆኑም መጽሐፉ መንፈሳዊ እንደመሆኑ መጠን ሁለት ነገሮች በእምነት ሲፈጸሙ ትርጓሜው ከንጋት ይጠራል። 2ኛ ጴጥ 1፥20 እነርሱም፥
መጽሐፍ ቅዱስ በሁለት አበይት ክፍሎች ይከፈላል። ይኸውም ብሉይ ኪዳን (Old Testament) ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፉ መጻሕፍት አዲስ ኪዳን (New Testament) ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሐዋርያት የተጻፉ መጻህፍት ናቸው።
ብሉይ ማለት የቆየ ጥንታዊ ማለት ሲሆን ኪዳን ማለት ደግሞ በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግ ስምምነት፣ ውል፣ መሀላ፣ ኑዛዜ፣ ቁርጥ ቃል ማለት ነው። ብሉይ ኪዳን ስንል የቆየ ጥንታዊ ቃል ኪዳን ማለት ነው። ይኸውም እግዚአብሔር አስቀድሞ ከእስራኤል ጋር የገባው ወይም የተዋዋለው ቃል ኪዳን ነው። (ዘፀ 24፥7) አምላክ ሠውን ከማፍቀሩ የተነሳ የሰውን ልጅ ሁሉ እንደባልንጀራ አድርጎ መሐላን ምሏልና ቃልኪዳንም ገብቷልና። (ዘፍ 22፥16-17፣ ዘፀ 22፥11፣ መዝ 10፥4 ዕብ 6፥13፣ 7፣21)
ብሉይ ኪዳን መባሉ በኋላ በክርስቶስ ደም የተመሰረተ ሌላ አዲስ ኪዳን ለእስራኤል ዘነፍስ ስለተሠጠ ነው። (ሉቃ 22፥20፣ ቆሮ 11፥25)
እግዚአብሔር አዲስ ኪዳንን እንደሚሠጥ በኤርምያስ አስቀድሞ ተናግሯል። (ኤር 31፥33)። ይሁን እንጂ ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን የማይነጣጠሉ አንድ ናቸው። ምክንያቱም ብሉይ ኪዳን ትርጓሜ ነውና። ብሉይ ኪዳን የአዲስ ኪዳን ትንቢት ሲሆን አዲስ ኪዳን ደግሞ የብሉይ ኪዳን ፍጻሜ ነው። ብሉይ ኪዳን መነሻ አዲስ ኪዳን መድረሻ ነውና።
አውግሰጢኖስ የተባለ ሊቅ ሲናገር አዲስ ኪዳን በብሉይ ኪዳን ተሰውሮአል። ብሉይ ኪዳንም በአዲስ ኪዳን ተገልጾአል ብሎአል።
እንግዲህ ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን እንደማያቋርጥ የወንዝ ውሃ ፈሳሽ አንዱ አንዱን እንዲሚስበው ሐረግ አንደኛው በአንዱ እንደታሰረ ሠንሠለት የታሪክ እና የዕምነት ትስስር አላቸው። አንዱ ያለአንዱ እንደማይቆም የሕንጻ ካብ ሁለቱ ኪዳናት ተደጋግፈዋል።
ስለዚህ ስብከታችን ከብሉይ ኪዳን ተነስቶ ወደ አዲስ ኪዳን ሲመጣ ዘላለማዊነትን ያገኛል።
መጽሐፍ ቅዱስ የኪዳናቱን ትስስር ጥላና አካል፣ ምሳሌ እና እውነት፣ ትንቢትና ፍጻሜ እያለ ይገልጸዋል። (ቆላ 2፥16-20፣ ዕብ 10፥1፣ ሉቃ 24፥44፣ ዕብ 8፥5)
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በይዘታቸው በአራት ይከፈላሉ። እነርሱም፦
የቀሩት አራቱ መጻሕፍት የሕጉ መጻሕፍት ናቸው። እነዚህ የሕግ መጻሕፍት የያዙት ሕግን ብቻ ሣይሆን እግዚአብሔር ከግብጽ ጀምሮ ከነዓን እስከሚገቡ ድረስ በአህዛብ ላይ ያደረገውን መቅሰፍትና ለእስራኤል ያደረገውን ተአምርና የሠጣቸውን ነፃነት ዘርዝረው ይናገራሉ።
አምስቱ የቅኔ መጻሕፍት ጊዜን፣ ኃይልን፣ ሕይወትን ከአንድ ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ የሚመክሩ ናቸው። መጻሕፍቱ አንድን ሰው ጥበበኛ ለማድረግ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን፣ የተግሣጽ ቃላትን እና መጽናናትን የሚያስገኝ ትምህርቶችን ይዘዋል። እነዚህ ጽሑፎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በጣም ተወዳጅ የሆኑ ክፍሎች አሉዋቸው። ስለዚህ አበው “መቅድመ መሀርዎሙ ለውሉድክሙ መዝሙረ ዳዊት ወምሳሌያተ ሰሎሞን” ብለው አዝዘዋል።
መጽሐፈ ኢዮብ የቀረበው በድራማ መልክ ነው። መጀመሪያው በስድ ንባብ ሲሆን ሌሎች የተዘጋጁት በግጥም ነው።
► መጽሐፈ ምሣሌ፥ ለትምህርትና ለተግሣጽ
► መጽሐፈ ዳዊት፥ ለምስክርና ንዑ ደቂቅየ…
► መክብብ፥ ፍልስፍና ሲሆን በዚህ ዓለም ያለው ማንኛውም ነገር ከእግዚአብሔር ውጭ ከሆነ የማይጠቅም መሆኑን የሚገልጽ ነው። ማስጠንቀቂያም ጭምር ነው።
ሀ. በብሉይ ኪዳን
1. ሕግ ዕዝ 10፥3፣ ነህ 8፥2፣ 7፥14፣ 10፥34፣ 31፥3
2. የሕግ መጽሐፍ ኢያ 1፥8፣ 8፥34፣ 1 ነገ 22፥8፣ ነህ 8፥3
3. የሙሴ ህግ መጽሐፍ ኢያ 8፥31፣ 23፥6፣ 2 ነገ 14፥6
4. የሙሴ መጽሐፍ ዕዝ 6፥18፣ ነህ 13፥1
5. የእግዚአብሔር ሕግ ዕዝ 7፥10፣ 1 ዜና 16፥40፣ 2 ዜና 31፥3
6. የእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ነህ 8፥18፣ 2 ዜና 17፥9
7. የእግዚአብሔር ባርያ የሙሴ ሕግ ዳን 9፥11-13፣ ሚል 4፥4
ለ. በአዲስ ኪዳን
1. የሕግ መጽሐፍ ገላ 3፥10
2. የሙሴ መጽሐፍ ማር 12፥26
3. ሕግ ማቴ 12፥25፣ ሉቃ 16፥16
4. የሙሴ ሕግ ሉቃ 2፥22፣ ዮሐ 7፥23
5. የእግዚአብሔር ሕግ ሉቃ 2፥23
6. ሙሴ ሉቃ 16፥30-31
በዚህ ዘመን የተፃፉ መጻሕፍት 46 ሲሆኑ የዘመኑ ጠቅላላ ብዛት 5500 ዓመታት ነው። ሲራክ 24፥ 6፣ ቀሌምንጦስ (በሐሙስ እለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ አምወለተ ወለትከ…) መዝ 89፥4 (እስመ አሠርቱ ምዕት ዓመት በቅድሜከ ከመ ዕለት …) ይህን አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን ለአራት ንዑሣን ከፍለን እናየዋለን።
ዘመነ አበው የሚባለው ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ አባት (እንበረም) ድረስ ያለው ሲሆን እነዚህንም አባቶች ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 5 እና 10፣11 ስናነብ የምናገኛቸው ሲሆኑ የዘር ሀረጋቸውም እንደሚከተለው ነው።
አዳም —> ሴት —> ሔኖክ —> ቃይናን —> መላልኤል —> ያሬድ —> ሄኖክ —> ማቱሳላ —> ላሜህ —> ኖህ —> ሴም —> አርፋክስድ —> ቃየንም —> ሳላ —> ኤቦር —> ፋሌቅ —> ራግው —> ሴሮህ —> ናኮር —> ታራ —> አብርሃም —> ይስሃቅ —> ያዕቆብ —> ፋሬስ —> ኤስሮም —> አራም —> አሚናዳብ —> ነአሶን
► ከአዳም – ኖህ አስር ትውልድ = 2242 ዓመታት
► ከኖህ – አብርሃም 11 ትውድል = 788 ዓመታት
►ከአብርሃም – ክርስቶስ 43 ትውልድ = 2470 ዓመታት
ኤጲፋንዮስ በአክሲማሮስ ዘመነ አበውን ሲጠቅስ ከአዳም እስከ ነአሶን ያለው ነው ብሎታል።
በዚህ ዘመን ከነበሩት አባቶች መካከል ሰባተኛው ትውልድ የነበረው ሄኖክ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል (መጽሐፈ ሄኖክን) እንደጻፈ ይታመናል። ዘመኑም 1486 ዓመተ ዓለም ነበር።
ይህ ዘመን ከሙሴ – ንጉሱ ሣኦል አባት (ቂስ) ድረስ ያለው ሲሆን በዚህ ዘመን 17 መሳፍንት በየጊዜው እየተነሱ እስራኤልን ከጠላት በእግዚአብሔር ኃይል ታድገዋል።
መሳፍንት ማለት ፈራጆች (አስተዳዳሪዎች) ማለት ሲሆን እራሱን የቻለ አንድ መጽሐፍ ስለመሳፍንት (በመሳፍንት) ስም ተሰይሟል። መጽሐፉ “መጽሐፈ መሳፍንት” በመባል ይጠራል። የመሳፍንት ታሪክ ከኦሪት ዘፀዓት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁ፣ ዘዳግም፣ ኢያሱ፣ መሳፍንት፣ ሩት፣ 1ኛ ሳሙኤል እናገኛለን። በዚህ ዘመንም እንደተፃፉ የሚታመኑት ኦሪት ዘፍጥረት፣ ኦሪት ዘፀዓት፣ ኦሪት ዘሌዋውያን፣ ኦሪት ዘኁልቁ፣ ኦሪት ዘዳግም፣ መጽሐፈ ኢያሱ፣ መጽሐፈ መሣፍንት፣ መጽሐፈ ሩት እና 1ኛ ሳሙኤል ናቸው። የመሳፍንቱ ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው።
ይህ ዘመን ከንጉስ ሳኦል እስከ ንጉስ ዘሩባቤል ድረስ ያለው ሲሆን በዚህ ዘመን የተለያዩ ነገስታት በእስራኤል እና በይሁዳ እየነገሱ ሕዝቡን መርተዋል። ነገስታቱ የተለያየ አመለካከት ስለነበራቸው አንዴ ወደ እግዚአብሔር ቤት አንዴ ወደ ጣኦት ቤት በመመላለስ ሕዝቡን ግራ ያጋቡ ነበር።
ሕዝቡም እንደ ንጉሱ አጎንብሱ ነውና አንዴ እግዚአብሔርን ሲያስደስቱ አንዴም ደግሞ ያሳዝኑ (ያስቆጡ) ነበር። ስለ ነገስታቱ የሚተርኩት መጻሕፍት የሚከተሉት ናቸው።
ሀ/ 1ኛ ሳሙኤል ለ/ 2ኛ ሳሙኤል ሐ/ 1ኛ ነገስት መ/ 2ኛ ነገስት ሠ/ 1ኛ ዜና መዋዕል ረ/ 2ኛ ዜና መዋዕል
የነገስታቱም ስም ዝርዝር ከ1ኛ ሳሙኤል ጀምረን ስንመለከት የሚከተሉትን እናገኛለን።
ከላይ ከተዘረዘሩት የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ (ሳኦል፣ ዳዊት እና ሰሎሞን) እሥራኤልን (10ሩ ነገድን) እና ይሁዳን (2ቱ ነገድን) በአንድ ላይ ጠቅለው የገዙ ሲሆን ከሮብዓም ጀምሮ ያሉት ግን በሁለቱ ነገድ (በይሁዳ ግዛት) ኢየሩሳሌምን ዋና ከተማ አድርገው የነገሡ ናቸው። የክርስቶስ የዘር ሐረግም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ላይ የተጠቀሰው ይህን ይከተላል። ቀጥሎ ያሉት ደግሞ በእስራኤል (10ሩ ነገዶች) ሰማርያን ዋና ከተማ አድርገው የነገሱ ናቸው።
† በ4407 ዓ.ዓ መጽሐፈ ነገሥት ተጻፈ † በ4447 ዓ.ዓ መዝሙረ ዳዊት ተጻፈ
† በ4481 ዓ.ዓ መጽሐፈ ሰሎሞን ተጻፈ (መጽሐፈ ሲራክ ወሰሎሞን መግቢያ)
† በ4905 ዓ.ዓ እስራኤል ወደ ባቢሎን ወረዱና በ4975 ዓ.ዓ ከባቢሎን ወደ ሃገራቸው ተመለሱ።
(መጽሐፈ ሰሎሞን ወሲራክ መግቢያ)
በዚህ ዘመን እንደተጻፉ የሚታሰቡት ቅዱሳት መጻሕፍት የሚከተሉት ናቸው።
►1ኛና 2ኛ ሳሙኤል 1ኛና 2ኛ ነገስት
► ትንቢተ ዕንባቆም
► 1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕል
► ትንቢተ ሶፎንያስ
► መጽሐፈ አስቴር
► መጽሐፈ ሶስና
► መዝሙረ ዳዊት
► መ/ ጦቢት
► መጽሐፈ ምሳሌ
► መ/ ዮዲት
► ተግሣፅ
► ጸሎተ ምናሴ
► መጽሐፈ መክብብ
► መ/ ባሮክ
► መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን
► ትንቢተ ኢሣይያስ
► ትንቢተ ኤርሚያስ
► ትንቢተ ሕዝቅኤል
► ትንቢተ ዳንኤል
► ትንቢተ ሆሴዕ
► ትንቢተ አሞጽ
► ትንቢተ ሚክያስ
► ትንቢተ ኢዮኤል
► ትንቢተ አብድዩ
► ትንቢተ ዮናስ
► ትንቢተ ናሆም
► መዝሙረ ሠለስቱ ደቂቅ ወዘተ.
ይህ ዘመን ከዘሩባቤል (ዕዝ 3፥2) እስከ ልደተ ክርስቶስ (ዘካ 4፥7) ያለው ሲሆን በዚህ ዘመን ካህናት (ነቢያት) ሕዝቡን እየመከሩና እያፅናኑ የመሲሁንም መምጣት በተስፋ እየተጠባበቁ የኖሩበት ዘመን ነው። በዚህ ዘመን እንደተጻፉ የሚነገርላቸው ቅዱሳት መጻሕፍት የሚከተሉት ናቸው። እነርሱም ሲራክ፣ ሀጌ፣ ዘካርያስ፣ ሚልክያስ ወዘተ…
የመጽሐፍ ቅዱስን ፀሐፊዎች ራሱ መጽሐፉ ማንነታቸውን ሲገልጽ በመንፈሰ እግዚአብሔር እየተቃኙ ቅዱሳን ሰዎች (በመንፈስ ቅዱስ የተነዱ/ የተመሩ) ቅዱሳን መሆናቸውን ይናገራል።
ዘዳ 17፥18፤ 31፥13፤ ኢር 1፥10፣ 36፥2 ማቴ 5፥18፣ ሉቃ 16፥17፣ 2 ጴጥ 1፥20፣ ራዕ 1፥11
እነዚህ ቅዱሳን ሰዎች የተለያዩ ሥራዎችና አኗኗር የነበራቸውና በተለያየ ዘመንና ቦታ የነበሩ ናቸው።
ሙሴ – እረኛ፣ ኢያሱ – መስፍን፣ ሳሙኤል – ካህን (ነቢይ)፣ ዘካርያስ – ካህን፣ ማቴዎስ – ቀራጭ፣ ሉቃስ ሐኪምና ሠዓሊ፣ ኤርምያስ – ካህን፣ ሰሎሞን – ንጉሥ፣ ጴጥሮስ – ዓሳ አጥማጅ፣ ያዕቆብ – ዓሳ አጥማጅ፣ እንድርያስ – ዓሳ አጥማጅ ወዘተ…
የጸሐፊዎችን ዝርዝር ስሞች ሙሉ ለሙሉ ለማወቅ ባይቻልም ታዋቂዎቹንና ስማቸው በመጽሐፍ ላይ የተጠቀሱት እንደሚከተለው በዝርዝር ቀርበዋል።
በ2ኛ ጢሞ 3፥16-17 ላይ እንደተጻፈው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ወይም በመንፈሰ እግዚአብሔር የተጻፉ ናቸው እንጂ የሰዎች ሃሳብ አይደሉም።
በቅዱሳን ሰዎች እንደተጻፉ ቢነገርም እንዲሁ በራሳቸው ሃሳብ አመንጭተው አልጻፏቸውም፣ ግን በመንፈሰ እግዚአብሔር ተመርተው ጽፈዋቸዋል። (2 ጴጥ 1፥19-21)
የቅዱሳት መጻሕፍት ሥራ መለኮታዊ ነው። ይህም ማለት የሰዎች ቃልና የሃሳባቸው ፍሬ ሣይሆን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ከናፍር ያናገራቸው በሰዎች ብዕር ያጻፏቸው ናቸው ማለት ነው (ኢሣ 8፣ 16-21፤ 34፣ 16 ኤር 36 ይመልከቱ።
በሌላ አነጋገር መጻሕፍት ቅዱሳት ሁለት ደራሲ (አዘጋጅ) አላቸው። ሰው ሁለተኛ ደራሲ ሲሆን መጀመሪያው ደግሞ በእያንዳንዱ ደራሲ አድሮ ያሳሰበና የገለጠ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔር የፈለገውን እንዲጽፉ የመረጣቸውን ሰዎች ያነሣሣል። (ኤር 1፥5፤ ገላ 1፥15፤ ዘፀ 34፥27፤ ዘዳ 31፥9-24)
ሰዎችም ከእግዚአብሔር የተቀበሱትን ለሰዎች ያስተላልፋሉ። ሰዎች በሁለተኛ ደራሲነታቸው በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በጽሕፈት የመጣላቸውን ቃል አስተውሎ ጠንቅቆ በመያዝ አስተዋጽኦ አላቸው ከዚህ በስተቀር ለመናገርም ሆነ ለመጻፍ እግዚአብሔር የገለጠላቸውን እንጂ ከራሳቸው አመንጭተው እግዚአብሔር እንዲህ አለን በማለት አይናገሩም። ( ኤር 1፥7፤ ሕዝ 2፥7፣ አሞ 3፥7፣ 1ኛ ነገ 2፥27)
በ1956 ዓ.ም በጀርመናዊው በጆሐን ጉተንበርግ የሕትመት መሣሪያ ከመፈልሰፉ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በፀሐፍት አማካይነት በእጅ እየተገለበጠ ይባዛ ነበር። ይህም ለብዙ ዓመታት ያህል በትጋት ተሠርቷል። ፀሐፍቱም በእብራይስጡ “ያህዌ” የሚለው የእግዚአብሔር ስም ጋ ሲደርሱ ወደ መሬት ወድቀው ይሰግዱና እጃቸውን ታጥበው “ያህዌ” የሚለውን ስመ አምላክ ይጽፉ ነበር። እንዲህ ባለ ክብርና ጥንቃቄ እንዲጽፉ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ስንል መጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ ጥበቃ የተደረገለት መጽሐፍ መሆኑ ነው።
በ1947 ዓ.ም በሙት ባህር አካባቢ ከብት ይጠብቅ የነበረ አንድ የዓረብ እረኛ በማሰሮ ውስጥ የተቀመጡ የብሉይ ኪዳን መጻህፍት ጥቅልሎች አግኝቷል። ከመጽሐፈ አስቴር በቀር ሁሉም የብሉይ ኪዳን ክፍሎች በቁርጥራጭ ተገኝተዋል። እነዚህ ጥንታውያን ጽሑፎች በክርስቶስ ዘመን የነበሩ ጸሃፍት የገለበጧቸው መጻሕፍት መሆናቸው ተደርሶበታል። መቁርጥራጮቹም የኢሣይያስ መጽሐፍ አሁን ካለው መጽሐፍ ጋር ማስተያየት ተደርጎበት ሙሉ በሙሉ የአሣብ አንድነት ተገኝቶበታል። በዚህም ሁለት ነገሮች
መልስ አግኝቷል።
በዓለም ላይ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጠላቶችን ተቋቁሞ የኖረ መጽሐፍ አይገኝም። ጠላቶቹም ተራ ሰዎች ሣይሆኑ ነገሥታትና ጳጳሳት፣ ፈላስፎችና ከሃዲያን ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ለዓለም (ለሰው ልጆች) የተሰጠው በእስራኤል በኩል ነው። እስራኤል ደግሞ መጽሐፉን ለቤተ ክርስቲያን እስክታስረክብ ድረስ በመውደም በፍልሰት (በስደት) የተጎዳች አገር ናት። እስራኤል ሶስት ጊዜ ፈርሳ ሶስት ጊዜ ተሰርታለች። እስራኤል ስትፈርስ መጻሕፍቱም አብሮ የመቃጠልና የመማረክ ዕድል ገጥሞአቸዋል። ስለዚህ በባቢሎን ምርኮ (በ586 ዓ.ም ቅ.ል.አ) መጽሐፍ ቅዱስ ጥቃት ደርሶበታል።
በ70 ዓ.ም የኢየሩሳሌምና የታላቁ መቅደስ መቃጠልም የመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ጉዳት ነበር። በሐዋርያት ዘመንና ከሐዋርያት ዘመን በኋላ የተነሱ መናፍቃን፣ መልእክት ባልጻፉ ሐዋርያት ስም “የእገሌ ወንጌል” በማለት ፍጹም የኑፋቄ መጻሕፍትን በማስገባት ሞክረዋል። ብዙ ዘመን ተሻግረን ሣንሄድ በ1526
ዓ.ም ዊልያም ቲንዲይል መጽሐፍ ቅዱስን በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመተርጎሙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ክብር በቋንቋ ሽግግር የጠፋ በማስመሰል በ1536 ዓ.ም በእሳት ተቃጥሎ እንዲገደል አድርጋለች። መጽሐፍ ቅዱስ ተከታዮቹን ብቻ ሣይሆን ራሱንም ለመከራ ያዘጋጀ መጽሐፍ ቢሆንም ጳውሎስ ያለው ግን ፀንቶ ይኖራል። መልእክተኞቹን እንጂ መልእክቱን ማሰር አይቻልም (2 ጢሞ 2፥9) በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተነሡ ብዙ ፈላስፎችም “መጽሐፍ ቅዱስ ከእንግዲህ ወዲህ የሚያነበው የለም” ብለው ነበር። በሚገርም ሁኔታ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከቤተ መቅደስ ንብረትነት ወጥቶ የእያንዳንዱ ሰው የግል ሀብት ደግሞም የቅርብ ጓደኛ የሆነው ከዚህ ጠቢባን ነን ባዮች ንግግር በኋላ ነው።
በአሁን ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ከ2800 ቋንቋዎች በላይ ተተርጉሟል። በቢሊዮን የሚቆጠሩ ኮፒዎችም በዓለም ላይ ተሰራጭተዋል። ይህን ያህል የቋንቋዎች ስፋንና የህትመት ብዛት ያገኘ ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀር ሌላ መጽሐፍ የለም። በአለም ላይ በሚገኙት ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴሎች መጽሐፍ ቅዱስ በእንግዳ ማረፊያ ክፍል ይቀመጣል። የክርስቲያን ደሴት በተባለችው በኢትዮጵያ ግን በማረፊያ ክፍል መጽሐፍ ቅዱስ ሣይሆን የኃጢአት መሣሪያ ነው የሚቀመጠው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለሰዎች መስክሯል። ሰዎችም ስለመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ሰጥተዋል። ለምሣሌ፦ ዩኒቨርስቲ ገብቶ መማር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ። ነገር ግን ዩኒቨርስቲም ባይገቡ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የሚገኘውን እውቀት ዩኒቨርስቲ ገብቶ መጽሐፍ ቅዱስን ሣያውቁ ከሚመረቁበት እውቀት እጅግ በጣም የተሻለ ነው። (ፕሮፌሰር ዊልያም ሊዮን)
መጽሐፍ ቅዱስ ለዓለማችን ጥያቄ ብቸኛው መልስ ነው። የሂንዱ እምነት ተከታይ የነበሩት ጋንዲ ለአንድ የብሪታኒያ መሪ (ባለስልጣን) “የእኔም ሆነ የእርስዎ አገር ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ በገለጸው ትምህርት ቢመሩ የሁለታችንም አገሮች ችግሮች ብቻ ሳይሆን የመላውን ዓለም ችግሮችን ለመፍታት እንችላለን” ብለዋል።
“መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አእምሮንና መንፈስን ወደሚያድስ ለምለም ስፍራ እንደመጓዝ ነው” (አንድ ሰው)
“መጽሐፍ ቅዱስ ዜጎችን በሙሉ ቀና ያደርጋል።”
ሣይንቲስት ሚካኤል ፋራዳይ “ለምን ይሆን ሰዎች በተሳሳተ አቅጣጫ ሕይወታቸውን የሚመሩት የተባረከው ቅዱስ መጽሐፍ በቀና ጎዳና ሊመራቸው መቻሉን አልተረዱት ይሆን?” ብለዋል።
ጆርጅ ዋሽንግተንም “ያለ እግዚአብሔርና ያለ መጽሐፍ ቅዱስ በትክክለኛ ፍትሕ ዓለምን መምራትና ማስተዳደር በፍጹም አይቻልም” ብለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ተነዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ አስተማማኝ መልሕቅ ነውና።
ታዋቂዋ ዶክተር ሄለን ኬለር “በሐሴት ስንሞላም ይሁን ስናዝን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ መቻል ይኖርብናል። ያለበለዚያ ሕይወትን አቻችለን ለመመራትም ሆነ ለመቋቋም አቅም አይኖረንም” ብላለች።
ዶክተር ሃዋርድ ኬሊ የተባሉ ሰውም “ሰይጣን ሰዎችን ሙሉ በሙሉ አሸንፎ ከቁጥጥሩ በታች የሚያውለው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡና እውነትን ከውስጡ እንዳይፈልጉ ልባቸውን ከዘጋ በኋላ ነው” ብለዋል