በአሪዞና ፊኒክስ እና አካባቢዋ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መኖር ከጀመሩ ከአራት አስርት አመታት በላይ ይሆናል። ማንም ክርስቲያን አካባቢውን ሲቀይር ቤተክርስቲያን ይኖር ይሆን ብሎ መጠየቁ የተለመደ ነው። ሆኖም በወቅቱ የኢትዮጵያውያን ቁጥር ጥቂት በመሆኑና የመገናኘት እድልም ስላልነበረ ሁሉም በየቤቱ ከመጸለይ በላይ ምንም ማድረግ አልቻሉም ነበር። ቤት ከመቀመጥ ደግሞ ቋንቋው ባይገባቸውም ከምንም ይሻላል በሚል ግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም እየሄዱ ይገለገሉ ነበር። በዓይን ከመተያየት አልፎ ሰላምታ መለዋወጥ ብሎም ወደ መመካከር የዘለለው የኢትዮጵያውያኑ ግንኙነት በቋንቋቸው ወደመገልገል ተሸጋግረዋል።
ወልደው እንኳን ልጆቻቸውን ለማስጠመቅ ይቸገሩ እንደነበር የሚናገሩት የዚህች ቅድስት ቤተክርስቲያን መስራቾች በሁለት እግራቸው ለመቆም ብዙ ተቸግረዋል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ተጨምሮበት እ.ኤ.አ በ1999 ዓ/ም የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተመሰረተች። የራሷ መተዳደሪያ ደንብም ቀርጻ፣ በአሪዞና ስቴት ህጋዊ ሰውነትን አግኝታ ከተቋቋመች 23 ዓመታትን አስቆጥራለች ።
በጥቂት ብርቱ ምዕመናን የተቋቋመችው ይህች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ከ200 በላይ አባላት ያሏት ሲሆን፣ አገልጋይ ካህናት አባቶች፣ ወጣት ዲያቆናት እና ታዳጊ ህጻናት በአገልግሎት ይሳተፋሉ።
በእለተ ሰንበት እና በዓበይት በአላት በነጻነት በገዛ ቤተ ክርስቲያንዋ ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት ለማከናወን የታደለችው ቤተ ክርስቲያናችን ህጻናትን የቋንቋና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ታስተምራለች፣ ዲያቆናት እና እጩ ዲያቆናት የዲቁና ትምህርት ይማራሉ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እና ያሬዳዊ ዝማሬ ያጠናሉ።
ቤተ ክርስቲያናችን ጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ ብትሆንም ዛሬም መሟላት የሚገባቸው ሁኔታዎች እንዳሉን አውቀን ጠንክረን በመስራት ላይ እንገኛለን። ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት እንዲጨመርበት እና ሃሳባችን የተሟላ እንዲሆን በጸሎታችሁ እና በእውቀታችሁ እንዲሁም በገንዘብ አስተዋጽኦ የምትረዱንን ሁሉ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች ከልብ እናመሰግናለን።