ጊዜው የአሪዞና ዓየር ወደ ነበልባልነት የሚቀየርበት፣ ከሚከንፍ መኪና በቀር እግረኛ ለዓይን የማይታይበት፣ ዓየሯ ምግብ ከሆነባት እናት ኢትዮጵያ ለመጣ ደግሞ ሃገሩን ከገሃነመ እሳት የሚቆጥሩበት ሞቃት ግዜ ነበር::
ቅዳሴ፣ የቤተ ክርስቲያን እጣን ጭስና ዝማሬ የናፈቀው የሃገሬ ህዝበ ክርስቲያን መድረሻ አጥቷል:: ሐበሻ እዚህ ቦታ አለ ᎐᎐᎐ አዲስ ሰው መጣ ᎐᎐᎐ ሲባል የሚሮጥበት ᎐᎐᎐ ዘመድ ወገን፣ የሃገር የወንዝ ልጅ የሚናፈቅበት ዘመን ነበር::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ባልና ሚስት፣ ጓደኛ ውይይታቸው ሁሉ ቤተ እግዚያብሄርን ስለ ማግኘት ነበር:: እርስ በእርስ የሚተዋወቅ ᎐᎐᎐ጓደኛ ከዘመድ ተቆጣጥረው ተጠራርተዋል:: ቁጥራቸው ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው::
ያ ዘመን ሁለት ሆነው በካሴት ቅዳሴ ሥርዓት የተከወነበት፤ ከተከራዩበት አዳራሽ በ ”ሰዓት አልፏል” የሚባረሩበት፣ ገንዘብ ለመሰብሰብ በረዶና አይስ ክሪም ለመሸጥ ሲንከራተቱ ለገበያ ሳይበቃ በአሪዞና ቃጠሎ በረዶው ቀልጦ እናቶችን ለኪሳራ ያበቃበት ዘመን ነው::
ይህች ቤተክርስትያን ዛሬ ላይ ለመድረስ ምን መንገድ አልፋለች? አቀበትና ቁልቁለቱን እነማን አለፉት? ያን ዘመን ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት እንባ የሚቀድማቸው፣ በደስታ የሚመሰጡ፣ የዛሬን እድገት እንደ ህልም የሚያዩ አሉ:: እነዚህ ዕድለኞች ለመሆኑ የዛን ዘመን ችግር እንዴት አለፉት? የቤተክርስትያኗ የታሪክ አካላት ትውስታቸውን አጫውተውናል::
አቶ አባተ ድራር
እዚህ ያለን ምዕመናን ለሃይማኖታችን ያለን ጽኑ ፍቅር ይሄ ቤተክርስቲያን ከመመስረቱ በፊት ምን ያህል ያንገበግበን እንደነበር የሚረሳ አይደለም:: እስከ 1999 ድረስ ቤተ ክርስቲያን ለማቋቋም ብዙ ጥረት አድርገናል:: በተለያዩ ግዜያት የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች እየመጡ ያገለግሉን ነበር:: ጀምረው ጥለውን የሄዱበትም ግዜ ነበር::
በዛ ዘመን ልጅ ወልደን ክርስትና ለማስነሳት የምንቸገርበት ወቅት ነበር:: ለዚህ አገልግሎትም ከሌላ ስቴት ድረስ ቄስ ያስመጣንበት ግዜ ነበር:: በእነዚህ የችግር ግዜያት ሁልግዜ የራሳችንን እምነት የምንከተልበት የራሳችን ቤተክርስቲያን እንዲኖረን፣ ሥብሃተ እግዚያብሄር የምናቀርብበት ቦታ ለመመስረት ሁል ግዜ ጥረት እናደርግ ነበር::
ለአመታት ያደረግነው ጥረት ትንሽ ጭላንጭሉን ያየነው አባታችን አቡነ ጳውሎስ /ፓትርያርክ ከመሆናቸው በፊት/ ፊኒክስ መጥተው ነበር:: በዛ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በተገኘንበት ግሪክ ቤት ክርስቲያን አገልግለው ቅዳሴ ስርዓት አከናውነው ነበር:: በዛ ወቅት አባታችን ለግሪክ ቤተክርስትያን እንዲያግዙን እና እንዲተባበሩን በአደራ መልክ መልዕክት አስተላለፉልን:: ግሪክ ቤተ ክርስቲያን ከዛ በኋላ ለኢትዮጵያውያን የተለየ አመለካከት ነበራቸው:: የኃይማኖት አባቶች ሲመጡ የቤት ኪራይ በመክፈል፣ የተወሰነ የኪስ ገንዘብ በመክፈል ᎐᎐᎐ በተለያየ መልኩ ያግዙን ነበር::
የተደራጀ ማህበረሰብ ባለመኖሩ እና የገንዘብ አቅምም ስላልነበረን ቄሶችን ይዘን ቤተክርስቲያን ማቋቋም አልቻልንም::
ካህናት ለአገልግሎት መጥተው እኛ የተደራጀን ባለመሆናችን፤ ከእኛ በቂ ጥቅም ማግኘት ስለማይችሉ ጥለውን ይሄዱ ነበር::
እዚህ ደረጃ ለመድረስ እንደባለውለታ ልናስታውሳቸው የሚገባ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱልን ግለሰቦች አሉ:: ለምሳሌ አባ አዲስ አንዱ ናቸው:: በነጻ ብቻ ሳይሆን ከኪሳቸው ገንዘብ እያወጡ በማገዝ ያገለግሉን ነበር::
ሌላው ቄስ መኮንን ናቸው:: በአንድ ወቅት በጣም በተቸገርንበት ወቅት ከእግዚያብሄር የተሰጡን ትልቅ አባት ናቸው:: እንደውም ከ20 በላይ መዘምራኖችን ከሂዩስተን በአውሮፕላን ተሳፍረው ይዘውልን መጥተዋል:: ሁሉም እነታደሰ ቤት ነበር ያረፉት:: ምዕመናኑን በመንፈሳዊ መንገድ ገነቡት:: ገንዘብ መዋጮ በሚኖር በበዓል ግዜ እንኳን ያዋጡ ነበር::እንዲሁም ዘማሪ ይልማን የመሳሰሉ አንዳንድ አስተማሪዎችና ዘማሪዎች አስተዋጽኦ አድርገውልናል:: ዋናው መሰረታዊው የዚህ ቤተክርስቲያን እዚህ ደረጃ የመድረስ ሚስጥር ግን ህብረተሰቡ ለኃይማኖቱ ለዕምነቱ ያለው ከፍተኛ ፍቅር ነው:: ህዝቡ ያለው ፈሪኃ እግዚያብሄር፤ ልዩነታችንን ለአንድነታችን ብለን ዘርና ፖለቲካን ወደጎን መተዋችን፤ በመቻቻልና በቀናነት ለቤተክርስቲያኒቱ ብቻ በማሰብ የምናደርገው እንቅስቃሴ ነው::
እንደወንድማማችና እንደ ቤተሰብ መተያየታችንን፣ የቀረበ ግንኙነታችንን በምንም ምክንያት ማጣት አንፈልግም:: ይህ እንግዲህ የእግዚያብሄር ፈቃድ ነው:: ባንሰባብ ኖሮ ይህ መቀራረብ አይኖርም ነበር:: አሁን ከተቀራረብን በኋላ ደግሞ በምንም መስዋዕትነት አንድነታችንን መበታተን አንፈልግም:: በመካከላችን በጣም የጠበቀ ፍቅርና አንድነት አለን::
ሌላው ደግሞ በየወቅቱ የሚመረጥ ኮሚቴ አለ:: አንዱ ችሎታ ሊኖረው ሌላው ችሎታ ላይኖረው ይችላል፤ ነገር ግን ሁሉም ሰው የሚሰራው በንጹህ ልቦናና በቀና አመለካከት ነው:: ሌላው በጣም የምንኮራበት ነገር ቢኖር በዚህ ቤተክርስቲያን ዕድሜ ገንዘብን
በተመለከተ ምንም አይነት ማጭበረበር ተፈጥሮ አያውቅም፤ አንድም ቀን አንድም ሳንቲም ጎድሎ ማንንም ጥርጣሬ ውስጥ አስገብቶ አያውቅም:: ፋይናንሽያል ኤክስፐርትስ የሉንም:: አካውንታንት የሉንም:: ነገር ግን በመተማመን እና እግዚያብሄርን በመፍራት ነው የምንሰራው:: በክፍለ ዘመኑ የሌለ አይነት አሰራር ነው ያለን:: ይህ ልዩ የእግዚያብሄር ስጦታችን ነው:: በጣም ኩራት አለን:: እስከዛሬ በእያንዳንዱ ኮሚቴ የተከወነው ንጹህ የሆነ አሰራር ነው::
ሌላው እንደ መልካም አካሄድ ልገልጸው የምፈልገው የመተዳደሪያ ደንባችንን የምንከተለው በሚገባ ነው:: በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ኮሚቴ በየጊዜው ይመረጣል:: ማህበረሰባችን በባህላችን መልካም አመለካከተና ቅን ልቦና ያለው ህብረተሰብ ነው::
ሌላው የተከተልነው አቋም ዋናው የስኬታችን ምንጭ ነው:: በገለልተኝነት አቋም መጽናታችን ተጠቃሚ አድርጎናል:: ለረጅም ግዜ ተወያይተን፤ ተመካክረን ነው ለውሳኔ የደረስነው:: አንድነታችንን መከፋፈል ስለማንፈልግ ነው የወሰንነው:: በመጀመሪያ ደረጃ እምነታችንን መከተል፤ ሁለተኛ አንድነታችን እና ወንድማማችነታችን፤ በመጨረሻ ደግሞ ሁሉንም እንደአመጣጡ ለመቀበል ወስነን ነው ገለልተኛ መሆንን የመረጥነው::
በሌላ በኩል ያለን አመለካከት ክህነት የእግዚያብሄር ነው:: የእግዚያብሄርን ክህነት ተሸክሞ ቤተክርስቲያናችን የመጣ በክብሩ ይስተናገዳል የሚል ነው:: በየትኛውም ወገን ያሉ ጳጳሳት ሲመጡ በክብር ተቀብለን ባርከውን አገልግሎት ሰጥተውን በክብር አስተናግደናቸው ይሄዳሉ:: ከስኬታችን መንገዶች ጥቂቶቹ እነዚህ ናቸው ብዬ አስባለሁ::
ወ/ሮ ዘውዲቱ መኮንን
አቡነ ጳውሎስ እንድንደራጅ ብዙ ምክር ለግሰውን ነበር የሄዱት:: ከሄዱም በኋላ ሁለት ግዜ ቄሶችን ልከውልን ነበር:: የት እንደደረሱ እንኳን ሳናውቅ ጥለውን ጠፍተዋል:: ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው ስናወራው ቀላል ይመስላል እንጂ እጅግ ከባድ እና ልብ የሚሰብር አጋጣሚዎችን አላልፈናል::
ዘለቀ የሚባል የቤተክርስቲያናችን አገልጋይ ነበር:: እኔ በህይወቴ አልረሳውም:: በአንድ ወቅት በተፈጠረብን ችግር ኃላፊነቱን ውስዶ ህዝቡን ሰብስቦ፣ ቤተክርስቲያኗን ከአደጋ የታደገ ወንድማችን ነው:: አንዳንድ ችግሮች ነበሩ ለሊቱን ቤተክርስቲያን አድሮ ቁልፉን ቀይሮ የህዝቡን አደራ ተወጥቷል:: በገንዘቡም በጉልበቱም ያደረገው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም:: ዛሬ በስራ ምክንያት ወደ ሌላ ስቴት ቀይሮ ቢሄድም ሁሌም ስሙን የምናነሳው የምናስታውሰው ወንድማችን ነው::
ወ/ሮ ስላስ ተስፋዬ
7 አቬንዩ ላይ እያለን አባ አዲስ የሚባሉ ቄስ ነበሩ የሚያገለግሉን:: አባ አዲስ ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ አንድ አስተዋጽኦ አበርክተዋል:: ሳንስማማ ቀርተን ብንለያይም ብዙ ጥረት አድርገውልናል:: ከአዳራሽ አዳራሽ፣ ከአንዱ የውጭ ሃገር ቤተክርስቲያን ወደ ሌላው በጣም ተንከራተናል::
እኔ በበኩሌ ለቤት ኪራይ እንኳ ብትረዳን ብዬ ለልጆች ኩኪ፣ ዶናት፣ ሻይ፣ አይስ ክሬም፤ ለአዋቂዎች ቡና በመኪናዬ እያዞርኩ እሸጥ ነበር:: ዛሬ ሲታሰብ ቢያስቅም በወቅቱ የሚያሳዝን የገጠመኝም ነገር አለ:: አንድ ግዜ ከአዳራሽ ውጭ ሜዳ ላይ ለነበረን ፕሮግራም ሃገሩ ሙቀት ነውና ከሻይና ቡና ይልቅ በረዶ አይስክሪም ይሸጣል ብዬ በመኪናዬ ሞልቼ መጣሁ:: ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ ለመሽጥ ከፈት ሳደርገው ግን አይስክሪምና በረዶ አላገኘሁም፣ የድንጋይ ያክል ጠጣር የነበረው በረዶ ወደ ውሃነት ተቀይሮ፣ የነበረው እንዳልነበር ሆኖ አገኘሁት:: ይህ የሆነው ከዓመታት በፊት ቢሆንም ዛሬም ድረስ ሁላችንም የምናስታውሰው ገጠመኝ ነው::
ቤተክርስቲያን መግዛት ደረጃ ደርሰን፣ በራሳችን ግቢ የፈለግነውን ለማድረግ መቻላችን እንደ ህልም ነው የሚታየኝ:: የፊኒክስ ነዋሪ ምዕመናን ሁሉ እግዚያብሄር ይስጠው:: ሁሉም ብዙ ጥረት አድርጓል:: እዚህ ደረጃ ያደረሰን እግዚያብሄር ይመስገን::
አቶ አርዓያ ታደሰ
እዚህ ከተማ ውስጥ 24 ዓመታት ኖርያለሁ:: የዛሬ 19 እና 20 ዓመታት ገደማ የራሳችን ቤተክርስቲያን ስላልነበረን ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈናል:: ልጆቻችንን ግሪክና ግብጽ ቤተ ክርስቲያን ነበር ክርስትና የምናስነሳው::
በተደራጀ መልኩ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ብዙ ግዜ ቤተክርስትያን ለማቋቋም ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም:: ቀኑን በትክክል መግለጽ ባልችልም በ1999 አባ አዲስ አንተነህ የተባሉ አባት አንድ ቤተክርስቲያን ፈልገው አግኝተው ሰዎች እያሰባሰቡ ጸሎት ያደርጉ ነበር:: በርግጥ በወቅቱ ብዙ ሰው አይሄድም ነበር:: አንድ ወቅት ላይ የትንሳኤ ምሽት በርካታ ምዕመናን በተሰበሰብንበት አባ አዲስና ሌላ ካህን በተገኙበት እጅግ ደስ የሚል ምሽት አሳለፍን:: በዚህ አለያም በዛ ምክንያት ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ቢሆንም በነበረው መልኩ አልቀጠለም::
በወቅቱ በፍላጎታቸው ተነሳስተው ኃላፊነት ወስደው ለማስተባበር የሞከሩ ሰዎች ነበሩ:: ስም መጥቀስ ቢያስፈልግ አቶ ታደሰ ኃብተየስ፣ ወ/ሮ ዘውዴ አበራ፣ ወ/ሮ ስላስ ተስፋዬ፣ ወ/ሮ አምሳለ ይገዙ፣ አቶ አበራ ታደሰ፣ ወ/ሮ ስመኝ መንግስቱ፣ አቶ አርዓያ ሽፈራው፣ ወ/ሮ ውብ አደይ በቀለ፣ ወ/ሮ አማረች ሃብተየስ፣ አቶ አባተ ድራር፣ አቶ አለምአየሁ አለምነህ እና ሌሎችም ነበሩ::
በአባ አዲስ አንተነህ አመራር ብዙ ስራ እየተሰራ ነበር:: ዲያቆናትና አስተማሪዎች ሰባኪዎች ስላልነበሩ በአቶ ግዛቸው ግርማይ እና በኋላም ዲያቆን ነብዩ የተባለ ወንድማችን መዘምራን በማሰባሰብ ብዙ ትብብር አድርገዋል:: የእነዚህ ሰዎች እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያኗ እውን እንድትሆን ብዙ አስተዋጽኦ ነበረው:: ሆኖም ነጻ ሆነን አልነበረም የምንንቀሳቀሰው::
ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆነን የተንቀሳቀስነው መተዳደሪያ ደንብ አውጥተን በአሪዞና ስቴት ህግ መሰረት ቤተክርስቲያኗ ህጋዊ ሰውነት ካገኘች በኋላ ነው:: ቅድስተ ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሚል ህጋዊንቷ በሃገሪቱ ደንብ ታወቀ ማለት ነው::
ህጋዊ ሰውነት ካገኘን በኋላም ብዙ ፈተናዎች ገጥመውናል:: የነበርንበት ቦታ አመቺ አልነበረም:: በተለይም ታቦተ ህጉን ለማስገባት አመቺ ስላልነበረ አባ አዲስን “ይህ ቦታ አመች ስላልሆነ የቤተክርስቲያን ቅርጽ ወዳለበት ቦታ እንሄድ:: ቦታ እንቀይር” ብለን ጠየቅናቸው:: እሳቸውም የራሳቸው አመለካከት የነበራቸው ሰው ስለነበሩ ጥያቄያችንን አልተቀበሉም:: እኛ ወጥተን ሄድን:: በዚህ መልኩ ከእሳቸው ጋ ተለያየን::
አዲስ ቤተ ክርስቲያን ተከራይተን መገልገል ጀመርን:: አገልግሎት የነበረን በዲያቆናትና ሰባኪያን ሲሆን አንዳንድ ግዜ ከሌላ ቦታ ካህን በማስመጣት ነበር:: ያለ አባት /ቄስ/ የቤተ ክርስቲያን በጣም ከባድ ነው:: በመሆኑም ከላስ ቬጋስ አባ ኃይለማርያም የተባሉ ቄስ አስመጣን:: የእሳቸው ጥረትም ብዙ አስተዋጽኦ ነበረው:: ቢሆንም ባላሰብነው እና ባልጠረጠርነው ቀንና ሰዓት፣ በዕለት ፋሲካ ጥለውን ሄዱ:: ቄስ በሌለበት በካሴት በዓሉን አሳለፍን:: ጊዜው 2002 ነበር::
ኪራይ እየበዛብን እና በተለያየ ያለመመቸት ቦታ እንቀያይር ነበር:: በዛ ወቅት ቤተክርስቲያን ለመግዛት ታሰበ:: የተጠራቀመ የተወሰነ ገንዘብ ነበረን:: እሱን አስይዘን ይሄን ቤተክርስቲያን ለመግዛት በቃን:: በአጭሩ እንዲህ ብለን እንግለጸው እንጂ እጅግ ፈታኝ የነበሩ፤ ተስፋ አስቆራጭ ሂደቶችን አሳልፈናል::
በኋላም አባ አብርሃምን አገኘን:: እጅግ ጥሩ አባት ናቸው:: ለሁሉም ጓደኛ፣ አባት፣ ወንድም ሆነው ነው የሚኖሩት:: እሳቸው ከመጡ በኋላ ምንም የገጠመን ችግር የለም::
የገለልተኝነት አቋማችንን በተመለከተ እኛ የፈጠርነው ፍልስፍና አይደለም:: ይህን ቤተክርስቲያን ለማስፋፋት ጥረት በምናደርግ ሰዓት ብዙ ሰዎች “ከማን ጋ ናችሁ?” የሚል ጥያቄ ያነሱ ነበር:: እኛ በዛ ሰዓት ይህን መልስ ለመስጠት ብንቸኩል ኖሮ ስራችን ሁሉ ይበተንብን ነበር:: “ከዚህ ጋ ነን”፤ አለያም “ይሄን አንፈልግም” አላልንም:: “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮች ነን” የሚለውን አቋም አጥብቀን መያዛችን ጠቅሞናል እንጂ አልጎዳንም:: በወቅቱ ያልገባቸው ወገኖች ሌላ ትርጉም ሊሰጡት ይችላሉ:: ይህ አቋማችን ቤተክርስቲያን ለመመስረት፤ ምዕመናን እንዲጠናከሩ እንዲተባበሩ ለማድረግ ጠቅሞናል::
ሁለተኛ፦ የተፈጠረ ጥፋት የለም:: ማንኛውም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስም መጥቶ ቀና የሆነ የቅዳሴ ስርዓት፣ ቀና የሆነ ትምህርት ላበረከተልን ሰው በክብር ተቀብለን በክብር ነው የሸኘነው:: ይህም ችግር ውስጥ አላስገባንም::
ትብብርን በተመለከት አቅም ያለውም የሌለውም፣ ሰርቶ ብዙ ገንዘብ የሚያገኘውም የማያገኘውም ሁሉም ተባብሮ በአንድ አቋም መቆሙ ነው ይህችን ቤተ ክርስቲያን እዚህ ደረጃ ያደረሳት:: ያሳለፍነውን ችግር ላላየ ሰው በቀላሉ እዚህ የተደረሰ ሊመስለው ይችላል:: ብዙ ውጣ ውረድ ነበረብን:: በሌለን ግዜ የነበረው ትንሽ ስጦታ እንደትልቅ የሚቆጠር ነበር::
በወቅቱ ከነበሩ ሁሌም ስማቸው የሚነሳ ሰዎች አሉ:: ለምሳሌ እማማ ስላስ ይትባረክ የተባሉ እናት $ 100.00 አውጥተው ያገለገለ ዕቃ የሚሸጥበት ቤት ማቀዝቀዣ ገዝተው አምጥተው ነበር:: ይህ አንዱ ምሳሌ ነው:: ዛሬ የምንገለገልበት ወንበር ከግለሰቦች እጅ ተዋጥቶ የተገዛ ነው:: ይህ አይነት ትብብር ባይኖር ኖሮ ይሄ ቤተክርስቲያን እዚህ ደረጃ አይደርስም ነበር::
አቶ ተሰማ ገብረ ክርስቶስ የተባለ ሰው ብዙ ግዜ ቤተክርስቲያን ባይመጣም ብዙ ትብብር ያደርግልን ነበር:: ወረቀት ማባዛት፤ መጽሄት ስንሰራ በራሱ ገንዘብ ሰርቶ አሳትሞ ያመጣልን ነበር:: ፋክስና ኮፒ ማሽን በስጦታ አበርክቶልናል::
ይህን ያነሳሁት በግለሰቦች መልካም ትብብርና አስተዋጽኦ እዚህ ደረጃ መድረስ መቻላችንን ለማስታወስ ነው:: በንጹህ ልቦና ሁሉም ተባብሮ የሚሰራው:: ለአንድ ጉዳይ እገሌ ብለን ብንጠራ ያለማወላወል መጥተው ነበር የሚከውኑት:: በዓል ብናከብር ሴቶቹም ወንዶቹም ሁሉም ተባብሮ፤ ግዜውን ገንዘቡን ሰውቶ ነው ትብብሩን የሚያሳየው:: ለምሳሌ ደህናሁን ደስታን ለአንድ ጉዳይ ብንፈልገው እና ብንደውልለት ስራውን ትቶ በተጠራበት ሰዓት ይደርሳል:: ጋሽ አርአያ ለቤተክርስቲያን ጉዳይ ሲሯሯጡ አደጋ አጋጥሟቸው ትከሻቸው እስካሁን ስብራት አለባቸው::
ይህን ቤተክርስቲያን እዚህ ደረጃ ያደረሰው ገንዘብ ሳይሆን የሰዎች ፍቅር፣ የሰዎች ትብብር ፣ የሰዎች አንድነት ነው:: ያለዛማ ገንዘብ ብቻውን የማይሰራቸው ብዙ ትብብር የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ:: እኛ ብቻ ሳንሆን ከሌላ ስቴት በእንግድነት የሚመጡ ሰዎች ሁሉ “ፊኒክስ አሪዞና የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሌላ ሃገር ካሉ ኢትዮጵያውያን የተለዩ ናቸው:: ትብብራቸው ያስደስታል” ብለው ነው የሚመሰክሩልን:: ይህም በጣም ያኮራናል:: ይህን ባህላችንንም ለልጆቻችን እንደምናወርስ ተስፋ አደርጋለሁ:: አንድን ማኅበረሰብ ጠንካራ የሚያደርገው ልዩነቱን እንደ ልዩነት አስቀምጦ በአንድነት ሆኖ መስራቱ ነው::
ይህን ቤተክርስቲያን ለመግዛት አቶ ታደሰ ኃብተየስ ብዙ ሚና ተጫውቷል:: ብዙ ለፍቷል:: የዚህ ቤተክርስቲያን ባለቤት ለመሆን የበቃነውም እሱና እሱን መሰል ሌሎች ጠንካራ ሰዎች ባደረጉት አስተዋጽኦ ነው:: ይሆናል፣ መደረግ አለበት ብለው፣ ጉዳዩን የራሳቸው ጉዳይ አድርገው ተስፋ ሳይቆርጡ በመነሳታቸው ነው::
ኦዲተር ሆኜ ሰርቻለሁ:: ሳንቲም የጎደለበትን ግዜ ግን አላስታውስም:: አንድ ሰው የሆነ ጉዳይ ለማስጨረስ ቢላክ ከካዝና ወጥቶ አያስፈጽምም “ኧረ ችግር የለውም” ብሎ ነው ከኪሱ አውጥቶ የሚያስፈጽመው::
አባቶችን በተመለከተ ከአሁን በፊት ብዙ ችግር አይተናል:: አባ አብርሃምን የመሰለ አባት ለማግኘት ከባድ ነው:: በጣም ትልቅ አባት ናቸው:: ከትልቁ ትልቅ ሆነው፤ ከትንሹ ትንሽ ሆነው ከሁሉም ተግባብተውና ተከባብረው ሁሉንም በፍቅር ነው የያዙት:: እሳቸው የጠበቁት ሰላም ውጤቱን እያየነው ነው:: በርግጥ ለእምነታቸው ብለው ነው የሚያገለግሉት ቢሆንም ሁል ግዜም እናመሰግናቸዋለን::
አቶ ግዛቸው ግርማይ
ቄሱ ጥለው የሄዱበት አጋጣሚ መራር ቢሆንብንም ሕዝቡን ግን አጠንክሮታል:: ከዛ በፊት ብዙ ለፍተን ያልተሳካልን ሁኔታ ነበር:: ያ ክስተት ግን አጠንክሮን ከዛ በኋላ ነው ስኬታማ የሆንነው:: የቤት ኪራይ ለመከፈል፣ በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያኑን ለማስተካከል፣ የነበረው ሸክም ድካም እንኳ ማንም አይሰማውም ነበር:: ሰዓት ደረሰ ውጡ ስለምንባል ቶሎ ብለን ዕቃውን አንስተን፣ አዘጋጅተን እንወጣለን::
በኋላ ቄስ መኮንን አባ አብርሃምን ሲያመጡልን እንኳ ህዝቡ ስጋት ነበረው:: እኔ ያን ግዜ ስብከተ ወንጌል እሰብክ ነበር:: ነብዩ ወንድሜም አብረን ነበር የምናገለግለው:: “እናንተው ትበቁናላችሁ፤ የራሳችን ነገር እስኪኖረን ቄስ ይቅርብን” ነበር ሕዝቡ የሚለው:: ምክንያቱም የነበረን ልምድ ስጋት ላይ ጥሎናል:: እግዚያብሄር ይመስገን አባ አብርሃም ጥሩ አባት ሆኑልን:: እስከ ዛሬም በሰላምን በፍቅር አብረውን አሉ::
ወ/ሮ አምሳለ ይገዙ
አባ አዲስ ግሪክ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ግዜ ሰው ሰብስበው ቅዳሴ ሲያደርጉ ሄጃለሁ:: በ1999 የፋሲካ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይቋቋማል ተብሎ በስልክ ተነግሮኝ ሄጃለሁ:: በርግጥ ቦታው የባስኬት ቦል መጫወቻ ትልቅ አዳራሽ ነው:: በመጋረጃ ተጋርዶ ወንበር ተደርድሮ ቤተክርስቲያን መስሏል:: ሰው ጥሩ የፋሲካ ምሽት አሳለፈ::
በ2 ቄስ ነበር የሚቀደሰው:: በሚቀጥለው ሳምንት ለሁለት ተከፍሎ የተወሰነ ሰው ወደ ሌላ ቤተክርስቲያን ሲሄድ የተወሰንነው እዚሁ ማርያም ቀረን::
አባ አዲስን በዚህ አጋጣሚ አመሰግናቸዋለሁ:: ይሄን ሁሉ ህዝብ ያሰባሰቡት እሳቸው ናቸው:: እሳቸው ያንን ቦታ ለምነው ባያገኙልን መሰብሰብም አንችልም ነበር:: የነበርንበት ቦታ ቀን ቀን ልጆች የሚጫወቱበት አዳራሽ ነበር:: እሁድ እሁድ እኛ አጽድተን እንጸልይበታለን:: ኪራይ አንከፍልበትም ነበር::
በየሳምንቱ እሁድ መቼ በደረሰ ብለን በናፍቆት ነበር የምንጠብቀው:: ልጆቻችንም እዛው ሲጫወቱ ይውሉ ነበር:: ክረምት በሆነ ወቅት ዝናብ ሲዘንብ ቤቱ ስለሚያፈስ ብረት ድስት በየቦታው እየደቀንን ነበር የምንጠቀምበት::
አባ አዲስ ይህን ቦታ ከማስፈቀዳቸው በፊት ቤት የሌላቸው ሰዎች የሚያድሩበት ቦታ ነበር:: እኛ ቅዳሴ እናደርግበት የነበረው አዳራሽ በየሳምንቱ ቆሻሻ ወጥቶ ተጸድቶ እጣን ተጭሶበት ነበር ቅዳሴ የሚደረግበት:: እንደዛም ሆኖ ሠው ለመሰባሰብ ለቅዳሴና ለጸሎት በጣም ይናፍቅና ይጓጓ ስለነበር እንደ ቤተ ክርስቲያን ነበር የምንቆጥረው:: በጣም ብዙ ሠው ይመጣ ነበር::
በመሃከል ያለመግባባት ተፈጥሮ ነበር:: ያንን ቦታ ትተን ሌላ ቤተክርስቲያን ተከራይተን እንድንወጣ ሃሳብ ቀረበ:: ኮሚቴ ተቋቋመ:: ካሜልባክ ላይ አንድ ቤተክርስቲያን ተከራይተን እዛ መገልገል ጀመርን::
በዛ ወቅት ሁሌም የማልረሳው አንድ ነገር አለ:: ስላስ ተሸክማ መጥታ የምትሽጣቸው ነገሮች ነበሩ:: ሶዳ፣ አይስክሬም፣ በረዶ ላይ አስቀምጣ ትሸጥ ነበር:: በዛ በጠራራ ጸሃይ እዛ ቁጭ ብላ ስትሸጥ በረዶው ከነአይስክሬሙ ቀልጦ ተቀላቅሎ የሚጣልበት ግዜ ነበር:: ስላስ እንደዛ እያደረገች ለቤተ ክርስቲያን ገቢ ታስገባ ነበር::
እኛ ጸሎታችንን ቅዳሴያችንን ሳንጨርስ ሌሎች ከውጭ ለመግባት ቆመው ይጠብቁን ነበር:: አንዳንዴ በሩን ያንኳኩ፣ ይከፍቱብን ነበር:: ብዙ ረብሻና ያለመረጋጋት ቢኖርብንም እንኳ ባለችን አንድና ሁለት ሠዓት በጣም ተደስተን ነበር የምንለያየው::
ጸሎታችንን የምናደርገው ግዛቸውና ነብዩ በካሴት ቅዳሴ መዝሙር እያመጡልን ነበር:: ያ ቦታ ሳይሳካ እንደገና ወደ ቫንቡረን ገባን:: የተሻለ ቤተክርስቲያን ነበር:: በዛ ሠዓት አባ ኃይለማርያም የሚባሉ ቄስም አስመጣን፣ ቅዳሴም ይደረግ ነበር:: ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት ቤተመቅደስ ለማዘጋጀት ክፍሉን የምንከፋፍለው በመጋረጃ ነበር:: ያንን ለማዘጋጀት ሠዓት ይፈጅብናል:: ሁሉንም ነገር በሚገባ ሳንጨርስ ሠዓት ይሄድብን ነበር::
ቦታዋ በጣም ጠባብ ክፍል ብትሆንም ቅዳሴ ነበር:: በየ15 ቀኑ ትምህርት ነበር:: ቤቷ በእጣን ታፍና ደስ የሚል ነገር ነበረው:: ደጅ ስንወጣ ደግሞ አማረች፣ ስመኝ፣ ዘውዴ፣ እማማ ስላስ፣ ቁጭ ብለው እጣንና ጧፍ ሻማ ይሸጣሉ:: አካባቢው ሁኔታው ሁሉ ሃገር ቤት ያለን ነበር የሚመስለው:: ያ ሁሉ ቤተክርስቲያናቸውን ለማቋቋም ምን ያህል ትግል እንደነበራቸው ነው የሚያሳየው:: ይቺ ቤተክርስቲያን እዚህ ደረጃ የደረሰችው በእነሱ ትግል ነው::
ያንን ቦታ እንፈልገዋለን ብለው ደግሞ አስወጡን:: ከዛ ደግሞ ግብጽ ቤተክርስቲያን ገባን:: ስካስዴል ነበር:: ለብዙ ሰው ይርቅ ነበር:: ያም ሆኖ ሁሉም ሰው እንደምንም ብሎ ይመጣ ነበር:: ያ ሁሉ እንግልት ስላማረረን ቤተ ክርስቲያን ለመግዛት ወስነን ፍለጋ ጀመርን:: ቤተክርስቲያን ለመግዛት የነበረው ፍለጋ ራሱ ቀላል አልነበረም:: በፍለጋችን ወቅት እጅግ በጣም ውድ ይሆንብናል፣ የተሻለ ዋጋ ያለው ደግሞ ወይ ቅርጹ የማይሆን አለያም ፊቱ ወደ ምስራቅ ያልሆነ᎐᎐᎐ በአጠቃላይ ማሟላት የሚገባውን ባለማሟላቱ ብዙ ቦታ አይተን ሳይመረጥ ቀርቷል:: መጨረሻ ላይ ግን ይህችን ቤተክርስቲያን ስናገኝ በቂያችን ናት ብለን ለመግዛት ወሰንን::
ለረጅም ግዜ ተዘግቶ የኖረ ቤተክርስቲያን ስለነበር በጣም ጽዳት ይፈልግ ነበር:: ህዝቡ ተረባርቦ አስተካከለ:: ሲገዛ እንደዚህ አልነበረም:: ቤተመቅደሱን ራሳችን ነን የሰራነው። በተወሰኑ ሰዎች ስጦታ ምንጣፍ ገባ፤ መጋረጃ ተደርጎ ቤተክርስቲያን መሰለ:: ብዙ ችግሮችን ብናሳልፍም እዚህ ደረጃ በመድረሳችን እግዚያብሄር ይመስገን:: ዛሬ የቆምንበት ቦታ በጣም የሚያስደስት ስለሆነ ያ ትዝታ ሆኖ ያልፋል::
ያሳለፍነው ገጠመኝ ሁሉ ለልጆቻችን የምናወራው፣ ለራሳችን ደግሞ የምንመካበት ነገር ነው:: በጣም ጠንካራና ፍቅር የተሞላበት ቤተክርስቲያን ልናቋቁም ችለናል:: እዳችንን ከፍለን በተጨማሪ የገዛነው መሬት ዕዳ አልቆ የዚህ ሁሉ ንብረት ባለቤት ለመሆን በቅተናል:: የምዕመናን ቁጥርም በየዕለቱ እየጨመረ ነው:: በጣም ደስ ይላል::
በዚህ አጋጣሚ አንድ የማልረሳው ነገር መናገር እፈልጋለሁ:: አባ ኃይለማርያም ጥለውን በሚሄዱበት ሠዓት የተሠማኝ ነገር አለ:: በዛ ሠዓት ብዙ ምዕመናን ኩዳዴን አይጾምም ነበር:: እሳቸው አስተምረው በጣም ቅስቀሳ አድርገው፣ እንኳን እኛ ልጆቻችን እንዲጾሙ አድርገው፣ ሁሉም ሰው ጾሞ ፋሲካን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በጉጉት ነበር የምንጠብቀው:: በጤንነት ምክንያት ሊሄዱ ነው የሚባል ነገር ሰማን:: በጣም ደንግጠን ተሰብስበን ቤታቸው ድረስ ሄደን ለመንናቸው:: “እባክዎትን ሌላው ቢቀር ፋሲካን እንኳ አብረውን ዋሉ” ብለን ለመንናቸው:: ፋሲካን ሊውሉ እሺ ብለው ቃል ገቡልን:: ለህዝቡም ፋሲካን ይውላሉ ተብሎ ተነገረ:: እኛም የፋሲካን በዓል በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት ጀመርን::
እሁድ የፋሲካ ምሽት እኛ ፋሲካን ልናከብር፣ ልናስቀድስ፣ ጾም ልንፈታ ቤተክርስቲያን ስንሄድ እሳቸው የሉም:: የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ቁልፉን ለጋሽ አርዓያ ሰጥተው ኦክላንድ ገቡ ተብሎ ተነገረን:: ማንንም አልተሰናበቱም፤ በለሊት ተሳፍረው ሄጃለው ብለው ነው የደወሉት:: ሰው ሁሉ በጣም አለቀሰ በጣም አዘነ:: ትምህርታቸው ጥሩ ስለነበር በጣም ነበር የምንወዳቸው:: ነገር ግን በጣም አሳዘኑን:: ሆኖም ግን በደመቀ ሁኔታ በዓላችንን አከበርን::
ለእኛ ግን ትልቅ ጥንካሬ ነው የሆኑን:: ትልቅ ትምህርትም ነው የተማርንባቸው:: ከዛ በኋላ ቄስ ይመጣል ስንባል ራሱ መስጋት ጀምረን ነበር:: እግዚአብሄር ይመስገን አባ አብርሃም እስካሁን ከእኛ ጋ ናቸው::
ገንዘብን በተመለከተ ኦዲተር ሆኜ ሰርቻለሁ:: በጣም ነው የሚገርመኝ:: አንድም ግዜ ገንዘብ ጎድሎብን አያውቅም:: ኮሚቴ በየምክንያቱ ህዝብ ጋ ቀርቦ ገንዘብ መጠየቅ ስለማይፈልግ ተከፋፍሎ አዋጥቶ መክፈልን ይመርጣል:: በተለይ ጥቃቅን ወጪዎችን ኮሚቴው ተከፋፍሎ መሸፈንን እንደ ባህል አድርጎታል ማለት ይቻላል::
የቤተክርስቲያንን ገንዘብ መንካት የሚያስብም ያለ አይመስለኝም:: ሁሉም ፈሪሃ እግዚያብሄር ያለበት ነው:: በሃሳብ ልንፋጭ ልንጨቃጨቅ እንችላለን:: ስንወጣ ግን ሌላ ሰዎች ነን:: የተለያየ ሃሳብ ቢኖረን እንኳን የአብዛኛውን ሃሳብ በመቀበል ነው የምናጸድቀው:: ለዛም ነው በፍቅር የኖርነው፣ ቤተክርስቲያናችንም እዚህ ደረጃ የደረሰው::
አቶ ደህናሁን ደስታ
ይህች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ እዚህ ላይ ቆማ ለተመተከታት ያሳለፈችውን ችግር መገንዘብ ሊያዳግተው ይችላል:: ዛሬ ከሞላ ጎደል ብዙ ነገር ተሟልቷል:: ማስቀደስ፣ ቅዱስ ቁርባን መቀበል፣ ክርስትና ማስነሳት፣ አመታዊ በዓልን ማክበር፣ ኃዘን ቢደርስ አጽናኝ እናት ቤተክርስቲያን አለች:: ይህ ህዝብ እህትም ወንድምም ነው:: በስደት ላለ ህዝብ የራስ ወገንን በፍቅር ተሰባስቦ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም::
እኛ ብዙ ክፉ ቀናትን አሳልፈናል:: ቤተክርስቲያኗ ላይ የመጣ ችግር እኛንም በግል አግኝቶናል:: እኔ ቤቴ ትዳሬ ላይ ሳይቀር ችግሩ በደሉ ደርሶብኛል::
ደህና ተሰባስበን ቤተክርስቲያን ብለን ያገኘንበት ቦታ እግዚያብሄርን እናመልክ ነበር:: ይመጡ የነበሩ አባቶች ግን አስቀይመውን ነበር የሚሄዱት:: ቄስ ኃይለማርያምን ስናገኝ በጣም ነበር ደስ ያለን:: ጥሩ አባት ነበሩ:: በወቅቱ አስተምረው፣ገስጸው ነው ጾም እንኳን እንጾም የነበረው:: በፍቅርና በደስታ ነበር የምንሰባሰበው:: ሆኖም ባላሰብነው ሰዓት ጥለውን ሄዱ:: እጅግ ደነገጥን:: አለቀስን:: በአባቶች እምነት ማጣት ደረጃ ደረስን::
ቄስ መኮንን በየሁለት ሳምንቱ ቤታቸውን እየዘጉ ነበር የሚመጡት:: እግዚያብሄር ይስጣቸው ብዙ ረድተውናል:: ከአባ አብርሃም ጋ ያገናኝንም እሳቸው ናቸው::
ከዛ በኋላ ለሁለተኛ ግዜ ያሳዘነን ነገር ይህች ቤተክርስቲያን በጥቂቶች አሻጥር ልትፈርስ ነበር:: በህዝቡ ጥንካሬና በእግዚያብሄር ቸርነት እዚህ ደረጃ ተደርሷል::
አቶ አርዓያ ሽፈራው
እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ፈተና ነው ያሳለፍነው:: ከተጠጋንበት ቤተክርስቲያን ውጡ ተብለን የተባረርንበት ግዜ ነበር:: ከላስ ቬጋስ ካህን ይዘን መጥተን ነበር:: እሳቸው ጥሩ እያገለገሉን ነበር ግን ባላሰብነው ግዜ ጥለውን ሄዱ:: አስተምረውን ስጋ ወደሙ ተቀበሉ ብለው እኛም እሺ ብለናቸው፤ አንድ ቅዳሜ እራት አዘጋጅተን እንብላ ብለን ብንደውልላቸው ስልካቸው አይመልስም:: በጣም ሞከርነው:: በኋላ ምሽት 9 ሰዓት ላይ ደውለው “ቁልፉን እገሌ ጋ አስቀምጫለሁ፣ እኔ ሄጃለሁ” አሉኝ:: በጣም ደነገጥኩ:: ምንም ማድረግ ስለማልችል ቤተክርስቲያን ለተሰበሰበው ህዝብ ሄጄ ተናገርኩ::
ሰው ሁሉ አዘነ አለቀሰ:: ሰኞ ስግደት ሊጀመር ነው ቅዳሜ ጠዋት ጥለውን የሄዱት:: ከዛ ቄስ መኮንን ይረዷችኋል ስለተባልን ለእሳቸው ነገርናቸው:: ከ 20 በላይ መዘምራን ይዘውልን መጡ:: እነ ታደሰ ቤት አረፉ:: እዛው ተሰተናገዱ:: የካቶሊክ ቸርች ነበር የምንገለገለው::
አባ አብርሃምን በዚህ አጋጣሚ ነው ያገኘናቸው:: በዓሉን ለማክበር ከቄስ መኮንን ጋር መጥተው ነበር:: “እሳቸው ከእናንተ ጋ ይሁኑ” አሉን:: እሳቸውንም ለመኑልን:: አባ አብርሃምም እግዜር ይስጣቸው እሺ አሉ:: ከሚኖሩበት ሃገር እቃቸውን ጠቅልለው መጡ:: እዛ የተወሰነ ግዜ እንደተገለገልን አስወጡን::
ስካስዴል የግብጾች ቤተክርስቲያን ተከራይተን ነበር:: ቤተክርስቲያኑን ለእሁድ ዕለት እንፈልገዋለን አሉን:: የሰው ቤተክርስቲያን ነው:: አማራጭ የለንም:: ስለዚህ ቅዳሜ ቀን ለማስቀደስ ተገደድን:: አባ አብርሃምም በሁኔታው ተበሳጭተው ነበር:: “እስከዛሬ አመት ቤተ ክርስቲያን ካልገዛችሁ አብሬያችሁ አልቆይም” አሉን:: እኔ በሽተኛ ስለነበርኩ ማማከር እንጂ ብዙም አልሯሯጥም ነበር:: ታደሰ፣ ሰለሞን፣ ዘለቀ፣ አርአያ ነበር የተሯሯጡት:: ያ ሁሉ ልፋታቸው ግን መሬት አልወደቀም:: ሁልግዜም የጌታን ቤት የሚሰሩ ጥቂቶች ናቸው:: ተከታዩ መልካም መሆኑ ነው ውጤታማ የሚያደርገው::
ዛሬ ታዲያ ለዓመት በዓል ቤተክርስቲያኑ ግጥም ብሎ ምዕመናን ውጭ ሞልተውት ስመለከት እንባዬን ነው የሚያመጣብኝ:: ህዝበ ክርስቲያን ነጭ በነጩን ለብሶ አዳራሹን ሞልቶት ማየት እንዴት ያስደስታል? የኛ ችግር የዓመት በዓል ብቻ ነው ነጭ የምንለብሰው:: ነገርግን ሁሌም ቤተክርስቲያን ስንመጣ ጽድት ብለን መምጣት አለብን:: በሃገር ቤት እኮ የቤተክርስቲያን ልብስ የተለየ ነው፤ የትም አይለበስም:: በኋላ ሳጥን መጣ እንጂ የቤተክርስቲያን ልብስ በጋን ውስጥ ነበር በክብር የሚቀመጠው::
ይኸው የህዝብ መገልገያ ሆኗል፤ በተለይ ለኔና ለቤተሰቤ በጣም ነው የተጠቀምንበት:: አንደኛ ስጋ ወደሙን ተቀብዬበታለሁ:: ስድስት የልጅ ልጆቼን ክርስትና አስነስቼበታለሁ:: ልጄን በሞት ሳጣም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎልኛል:: ስራው ገና ብዙ ይቀረናል:: ወደ ፊት ደግሞ የበለጠ እንድንሰራ እግዚያብሄር ይርዳን::
አቶ ታደሰ ኃብተየስ
በዛ ዘመን ቤተክርስቲያን ስላልነበረን ልጆቻችንን ግሪክ ኦርቶዶክስ ነበር ክርስትና የምናስነሳው:: መቼም እግዚያብሄር በፈቀደ ግዜ ይህ ቤተክርስቲያን ተመሰረተ::
አባ አንተነህ ኢትዮጵያ ቅድስት ማርያም ብሎ ከ IRS መታወቂያ አስወጥተው ነበር:: ከሳቸው ጋ ሆነን ፈንድ ሬዝ እናደርግ ነበር:: ደረጀ እና በሪሁን የሚባሉ ልጆች ነበሩ በወቅቱ በሞራል እና በገንዘብ በጣም ነበር የረዱን:: ከችግራችን ብዛት ገንዘብ ለማሰባሰብ ማሲንቆ ተጫዋች ሳይቀር አስመጥተን ነበር:: እዛ ቤት ሆነን 40 ሺ $ ሰብስበን ነበር:: ያ ገንዘብ በእሳቸው እጅ ነበር::
በቅድስት ማሪያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስም ማስታወቂያ ማስወጣት ነበረብን:: አትራፊ ያልሆነ ድርጅት /non profit organization/ መሰረትን:: ገንዘቡን በተመለከተ ስንነጋገር አልተግባባንም ነበር:: በዛ መሃል አቶ አርአያ ሽፈራው ለዚሁ ጉዳይ ሲሯሯጥ የመኪና አደጋ ደረሰበት:: እሱ ሆስፒታል ተኝቶ ነው ገንዘቡን በቤተክርስቲያኗ ስም የባንክ አካውንት ከፍተን እኔና ስመኝ ባንክ ያስገባነው:: ከዛን ግዜ ጀምሮ ጥሩ ጉዞ ጀመርን::
ጠዋት 5 ሰዓት ተነስተን በስልክ እርስ በእርሳችን እንቀሳቀስ ነበር:: መቅረትማ አይታሰብም:: በፉክክር ነበር በጠዋት ተገኝተን አስፈላጊውን ነገር አዘገጃጅተን የምንገለገለው::
በርግጥ አባ አንተነህ ገንዘብ እንኳን አይቀበሉም ነበር:: ግን አስቸጋሪ ግዜ ነው ያሳለፍነው:: ባለመስማማት ስንለያይ እንገለገልበት የነበረውን ቤተክርስቲያን ለሳቸው ነው እንጂ ለእናንተ አይደለም የሰጠነው አሉን:: ከዛ ቫንቡረን ላይ ሌላ ቸርች ተከራየን:: እዛ ደግሞ ልጆቻችሁ ረበሹ …. እና ሌላም ምክንያት ሰጥተው አስወጡን:: እያለቀስን ወጣን:: በርግጥ ያ በደል እልህ ውስጥ ከቶን እንድንጠነክር አድርጎናል::
በጉዟችን ላይ ብዙ እንቅፋቶች ነበሩብን:: መተዳደሪያ ደንቡ ይሻሻል በሚልና በተለያየ ምክንያት ለመበጥበጥ የሞከሩ ነበሩ:: ይህን ቤት ስንገዛም አይገዛም ማን ሊከፍለው ነው ብለው አመጽ ያስነሳ ቡድን ነበር::
ከዛ 17ኛ አቬንዩ ላይ ሌላ ቦታ ተከራየን:: እግዚያብሄር አንድ ነገር ቀና ሆኖ ሲጀመር ብርታትም ይሰጣል:: የእያንዳንዱ ሰው ሞራል በጣም ነው የሚደነቀው:: ለደረሰብን ነገር ሁሉ እጅ አንሰጥም፣ ሞራላችንም አይነካም:: ብዙ የሚያስደነግጥ የሚያሳዝን ነገር ቢደርስብንም በእግዚያብሄር ተስፋ እናደርጋለን፤ ደግሞ በሙሉ ልብ ተነስተን እንጀምራለን::
ግብጽ ቤተክርስቲያን ራሱ እንግባ አንግባ ክርክር ነበር:: ከሁሉ ሳንሆን ከምንቀር እንግባ በሚል እዛ መገልገል ጀመርን:: እንደውም ለመጀመሪያ ግዜ ቤተክርስቲያናችን በተክሊል ያጋባችው እዛ ነው::
የቤት ግዢውን በተመለከተ ብድር ማግኘት ያስቸግር ነበር:: ምክንያቱም ድርጅት ስለሆነ የአባላት ቁጥር፣ ገቢ የመሳሰሉት ነገሮች ይፈለጉ ነበር:: ብዙ ባንክ ሞክረን አናበድርም ብለውን ነበር:: በኋላ እንደ አማራጭ ያቀረብነው ሃሳብ 10 ሰዎች እንዲፈርሙ ነበር:: ከbank of America ጋ በመነጋገር አስሩ ሰዎች ፈረሙ:: ህዝቡ በጣም ፈቃደኛ ነበር:: አስሩም በደስታ ነው የፈረሙት:: በርግጥ ከባድ ኃላፊነት ነበር:: ግን ሁላችንም ከእግዚያብሄር ጋ የቻልነውን ሁሉ እንጥራለን ብለን ነው የገባንበት:: እግዚያብሄርም ረዳን::
ወ/ሮ ስመኝ መንግስቱ
የተወሰንን ሴቶች ነበርን በየግዜው የምንሰራው:: ለፈንድ ሬዚንግ ምን እናድርግ ሲባል “ዘፋኝ እናምጣ” ተባለ::
“ማንን እናምጣ?” ….
“ወሴ ባሴ ይምጣ… ከሲያትል”
“የት ይረፍ?”
“እዚሁ እኛ ጋ ይደር” … ሁለት ቀን እኛ ጋ አደረ::
ጠላ፣ ጠጅ እቤት አዘጋጀሁ:: ሸጥን:: ጥሩ ብር አገኘንበት:: ክርስትና እንደሚያስነሳ ድመት በየቦታው እየተንከራተትን… በየአዳራሹ በየዳንስ ቤቱ እየተከራየን፤ ያላየነው መከራማ የለም:: እግዚያብሄር እመቤቴ ማርያም ረዱን:: ውሃ፣ ቡና… ሻይ እየሸጥን:: ብዙ ችለን ነው እዚህ ደረጃ የደረስነው::
አባ ኃይለማርያም ከላስ ቬጋስ ስናስመጣ ደግሞ አንዱ ችግር ማረፊያ ነበር:: ቤት እንዳንከራይላቸው ገንዘብ ልናወጣ ነው:: ስለዚህ ተማከርንና እዚሁ ከኛ ጋ ይቆዩ ተባለ:: አራቱ ልጆቼ አሉ:: ስለዚህ ሳሎን ቤታችንን ለሁለት ለመክፈል ወሰንን :: ሆም ዲፖ መክፈያ ፓርቲሽን ገዝተን ሳሎኑን ለሁለት ከፈልነው:: አንዱን ለእሳቸው አንዱን ለትልቁ ልጃችን አደረግነው:: ለሁለት ሦስት ወር ያህል እንዲህ ተቸግረን ነው ያሳለፍነው:: በኋላ ቤት ተከራይተው ወጡ፤ ከዛ ነው ጥለውን የጠፉት::
ፈንድሬዚንግ ያዘጋጀን ዕለት ደረጀ እና በሪሁን አንድ አንድ ሺ $ እናውጣና ቸርቹ እንዲያድግ እናድርግ ብለው ተነሱ:: የዛን ቀን ብዙ ገንዘብ ተሰበሰበ:: ለ4 ዓመት ያህል ገንዘብ ያዥ ነበርኩ:: ከ100 ሺ $ በላይ ነው ያስረከብኩት:: ራሷ ማርያም ናት ያቆመችው:: ሰው ብሩክ ነው:: አሪዞና ተባበረ:: በገንዘብ በጉልበት ተባበረ::
ወ/ሮ አማረች ሃብተየስ
1987 ነው ልጃችን የተወለደው:: ልጃችንን ክርስትና ያስነሳነው ግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ነው:: ግሪክ ቋንቋ ስለማንችል ሰው ሲቆም እንቆማለን፤ ሲቀመጡ እንቀመጣለን:: ቤተክርስቲያን ስለሌለ እሁድ እሁድ እዛ ነበር የምሄደው::
አንድ እሁድ ቀን ከስመኝ ጋ ተገናኝተን “ግሪክ ቤተክርስቲያን ሄጄ መጣሁ” ስላት “ኧረ እዚህ 7 አቬንዩ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተጀምሯል” አለችኝ::
የሚቀጥለው እሁድ አልደርስ ብሎኝ ነው ቀን ስቆጥር የደረሰልኝ:: ከዛም እሁድ በጠዋት ተነስቼ የጋገርኩትን ድፎ ዳቦ ይዤ፣ ነጠላዬን አጣፍቼ፤ እንደ ሃገር ቤት የተሰበሰበ ብዛት ያለው ሃበሻ ለማየት እየሮጥኩ ስሄድ፤ በቁጥር 7 ሰዎች ብቻ አገኘሁ:: ባስኬት ቦል የሚጫወቱበት አዳራሽ ነው::
ስመኝ በተቻላት መጠን ሻማዋን አብርታ፣ እጣኗን አጭሳ ቤተክርስቲያን አስመስላዋለች:: በር ላይ ደግሞ ትንሽ ጠረጴዛ አስቀምጣለች፣ የሚሸጡ መጽሃፎችን ደርድራለች:: ጸበል መጠጫ ብርጭቆ ደርድራለች፤ ብቻ ከሰው ማነስ በስተቀር በጣም ደስ የሚል ድባብ ነበረው::
ይህች ቤተክርስቲያን እዚህ የደረሰችው በእምነት ነው:: ገንዘብ ገቢው ወጪው ሁሉ በመተማመን፣ እርስ በርስ በመነጋገር ነበር የሚሰራው:: ሁሉም እድገቱን ለማየት ይጓጓ ስለነበር ያለውን እያበረከተ፣ እየሰጠ ነው እዚህ የተደረሰው::
ባለማወቅ እና ለእድገቱ በመጓጓት መደረግ የሌለበትን ነገር አድርገን አልፈናል:: ለምሳሌ ለገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ዘፋኝ አስመጥተናል:: ጸበል ለማደል እኛ ሴቶቹ እንነሳ ነበር::
ቤተክርስቲያኑ እዚህ የተደረሰው በእውቀት ሳይሆን በፍቅር፣ በእምነትና በፍላጎት ነው:: ተገናኝተን በጉጉት የምናወራው እንዴት የተሻለ ቤተ ክርስቲያን ይኑረን የሚለውን ነበር:: እግዚያብሄር ይመስገን ዛሬ እዚህ ደርሰን የብዙዎች መሰባሰቢያ መሆኑ ያኮራናል::
አቶ ዘለቀ ሜጎ
በግለሰብ ደረጃ ምንም ያደረኩት ነገር የለም:: ሁሉም የተደረገው ከወንድሞቼ ጋር በመግባባት ነበር:: የደረሰው ውጣ ውረድ ብዙዎች በስደት ዓለም የሚያጋጥማቸው የዕምነት ፈተና ነው:: ይህ ፈተና አማኙ በዕምነቱ ላይ ያለውን ጥንካሬ የሚፈተንበት፣ ለሃይማኖቱ ያለውን ፍላጎት የሚያሳይበትና የጽናት መለኪያ ነው::
ብዙዎቻችን ልጅ ሆነን እንደ ዲያቆናት አላደግንም:: ሃገር ቤት ቤተ ክርስቲያንን ከመሳለምና ከማስቀደስ ውጪ ውስጠ ሚስጥሩን አናውቀውም:: በመሆኑም እዚህ ቤተ እግዚያብሄርን ለማቆም ስንታገል ከዕውቀት ሳይሆን ከፍቅር፤ በብልጣብልጥነት ሳይሆን በየዋህነት ነበር የምንታገለው::
እኔ ከሃገሬ ስወጣ ትምህርት ላይ ነበር ትኩረቴ:: ከኮሚኒቲ ኮሌጅ በኋላ አሪዞና ስቴት ዩንቨርስቲ ነበር የሄድኩትና የጨረስኩት:: ትምህርቴን እስከምጨርስ ከህብረተሰቡ ጋ ብዙም አልተቀራረብኩም:: ራሴን ሳልችል ወደ ህብረተሰቡ ብቀርብ የማበረክተው የለም የሚል ስጋት ነበር የሚያርቀኝ::
እዚህ ሃገር በስደት ስንኖር እግዚያብሄር ሃይማኖታችን ላይ እንድንበረታ በጣም ነው የሚያግዘን:: ብዙዎች እንዲተባበሩን ልባቸውን ያራራልናል:: እነሱም የተቸገረ ለመርዳት ልባቸው ቅን ነው:: እኛ ሃገራችን ብንሆንና የሌላ ሃገር ሰው የሌላ ኃይማኖት ተከታይ ቤተ ክርስቲያናችንን ለመገልገል ቢጠይቀን እንሰጣለን? በፍጹም አናደርገውም:: እኛ ለሃይማኖታችን ቀናዒ ነን::
የእኛ ቤተክርስቲያን ስሙ ከተሰየመ በኋላ ነው የደረስኩት:: ባስኬት ቦል አዳራሽ እንገለገል ነበር:: አዳራሹን አስተካክለን፣ መጋረጃ ተደርጎ፣ ተዘጋጅቶ ነበር የምንገለገልበት:: በክረምት በጣም ሲበርድ በበጋ በጣም ይሞቅ ነበር::
የአባ አዲስ ውለታ መረሳት የለበም:: እግዚያብሄር በእሳቸው ተጠቅሞ ለእኛ በጎ ነገር አድርጎልናል:: መሰረቱ እሳቸው ናቸው ማለት ይቻላል:: አለመግባባት ነበር:: ከምዕመናን አስታራቂ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሰላም ለማስፈን ሁሉ ጥረት ይደረግ ነበር:: መግባባት አልተቻለም:: ከእሳቸው ተለይተን ለብቻችን መንቀሳቀስ ጀመርን:: ካቶሊኮች ጋ ተጠግተናል:: ልጆቻችሁ ረበሹ ተብለን ተባረርን::
ፓርቲ የሚደረግበት አዳራሽም ተገልግለናል:: ሲጋራውን መጠጡን አጽድተን እንገለገልበት ነበር:: በወቅቱ ከተለያዩ ስቴቶች ቤተክርስቲያናት ጋ ጥሩ ግንኙነት ነበረን:: አባ ኃይለማርያም መውደድ የተባሉ አባት ከላስ ቬጋስ አስመጥተን ያገለግሉን ነበር:: አባ ኃይለማሪያም ጥሩ የአስተዳደር ችሎታ ነበራቸው:: ዕርዳታ ማሰባሰብ ይችሉበታል:: በአጭር ግዜ ውስጥ ብዙ አስተዋጽኦ አድርገዋል::
ህዝቡ በፍቅር ነበር የያዛቸው:: ሁዳዴ ጾም ላይ እንደውም ህማማት ከገባ በኋላ ነው ጥለውን አሳዝነውን የሄዱት:: ከየትኛው ናችሁ? አቋማችሁን አሳውቁኝ በሚል ማምለጫ ጥያቄ ነው ጥለውን የሄዱት:: ህዝቡ እያለቀሰ ነው አመት በዓልን ያሳለፈው::
ይህን እንደ አንድ ፈተና ነው የማየው፤ ምክንያቱም በወቅቱ ተስፋ አስቆራጭ እና አሳዛኝ ዱብእዳ ነበር የሆነብን:: በዕምነታችን በጠነከርን ቁጥር ፈተና ይመጣል:: እምነታችንን አንተውም ብለን በተሰባሰብን ቁጥር ፈተናው በዝቶብን ነበር:: ለእሳቸውም ፈተና ነው ብዬ ነው የማምነው:: በጎቹን እንዲያግድ የተሰጠው እረኛ ነበሩ:: በጎቹን በአግባቡ የሚጠብቅ እረኛ ጌታውንም ያስደስታል:: ለምለም ሳር የመገበ፣ ውሃ ያጠጣ እረኛ በጎቹ ደስታቸውን ለጌታቸው ሲገልጹ እረኛው መልካም ስራ እንደሰራ ምስክር ይሆናሉ:: እሳቸው በጎቹን እንዲያግድ የተሰጠው እረኛ ነበሩ:: ፈተናውን አላለፉም፤ ጥለውን ሄዱ::
ምዕመናን ውስጥም ሁለት ሃሳቦች ነበሩ:: ለምን የአባ ጳውሎስ ስም አይነሳም? የሚሉ ነበሩ:: ሆኖም “በሲኖዶሱ ጉዳይ ገብቶ መፈትፈቱ የእኛ ጉዳይ መሆን የለበትም፤ አቅማችንም አይፈቅድልንም:: ጳጳሳት ኤጲስ ቆጶሳት የሚለው በህይወት ያሉትንም ያለፉትንም ሁሉንም ይወክላል” ብለው አስረዱን:: ጥሩ መካሪ ነበሩ:: አቶ አለማየሁ ይባላሉ::
በርግጥ እኔም እንደማስበው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳስተማረን ወደ ሮማ ስትሄዱ እንደ ሮማ ኑሩ ይላል:: እናም በሰው ሃገር በስደት ስንኖር እንደ ሃገራችን ሳይሆን እንደ ሃገሬው ነው የምንኖረው:: የዚህን ሃገር ህግና ደንብ ተከትለን ነው የምንኖረው:: ከአለባበስ ጀምሮ የቆምንባትን ምድር ህግ አስታርቀን መኖር ግዴታችን ነው:: የአሪዞና ህዝብ በርግጥ እድለኛ ህዝብ ነው:: ሁለቱንም አስታርቀን በጥበብ እና በብልህነት መቀጠላችን ሰላም እንዲሰፍን ነው የረዳን:: ሌላ ሃገር እኮ እስከአሁን በዚህ ጉዳይ ብጥብጥና ጸብ አለ::
ከምዕመናን ተሳትፎ የእናቶች አስተዋጽኦ እጅግ የሚደንቅ ነበር:: ወ/ሮ ስላስ ፈንድ ሬዝ ማድረግ የጀመሩት እሳቸው ነበሩ ማለት ይቻላል:: ሻይ እያፈሉ መሸጥ፣ ለህጻናት አይስክሬም… የመሳሰሉትን እየሸጡ ገቢ ያደርጉ ነበር:: ወ/ሮ አማረች ድፎ ዳቦ እየጋገረች ታመጣ ነበር:: ወ/ሮ ስመኝ…. ሌሎቹም የእናትነት ርህራሄያቸው፤ በእናትነታቸው ያደርጉ የነበረው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ነበር:: ቤተክርስቲያናችን አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰው በእነዚህ እናቶች ከፍተኛ ትብብር ነውና ቤተክርስቲያናችን የምትረሳቸው አይመስለኝም:: ከወንዶች አባቶችና ወንድሞች ከአቶ አርአይ አንስቶ እስከ ህጻናቱ ለዚህች ቤተክርስቲያን ብዙ ውለታ አድርገዋል::
ሌላው መረሳት የሌለባቸው ሰው ቄስ መኮንን ወልደጊዮርጊስ ናቸው:: ከሌላ ስቴት እየመጡ ይጎበኙን፣ ያጽናኑን ነበር:: አባ አብርሃምን ምዕመናን ፊት ጠይቀውልን ከእኛ ጋ እንዲቀጥሉ በሩን የከፈቱልን እሳቸው ናቸው:: ከእግዚያብሄር ጋር:: እኛ ለዚህች ምስኪን ቤተክርስቲያን እሺ ይላሉ ብለንም አልገመትንም ነበር:: እሺ ሲሉን በጣም ነበር የደነገጥነው ደስም ያለን:: ምክንያቱም ዙሪያው ገደል በሆነብን ሰዓት ነው እግዚያብሄር አባ አብርሃምን የሰጠን::
ከአባ አብርሃም ጋርም የተለያየ ቦታ ተንከራተናል:: ቤተክርስቲያን ለመግዛት የተወሰነው ከዛ በኋላ ነው:: ቦታውን ፍለጋም ከምዕመናን ጋ እንንከራተት ነበር:: ካየናቸው ቦታዎች ሁሉ የወደድነውን ቦታ ሌሎች ቀድመውን ገዙት:: መሬትም አግኝተን ነበር:: ቢዩልዲንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር:: አቅም ስላልነበረን መግባባትም አልተቻለም::
ይህ ቤተክርስቲያን ሲገዛም አቅጣጫው ላይ እና ሳውዝ አካባቢ መሆኑን አልወደድነውም ነበር:: ሳውዝ የጥቁሮች ሰፈር ነው የሚል ፍራቻ ነበር:: በኋላ ከአባታችን ጋ በመስማማት “ይሁን እግዚያብሄር የማያውቀው ነገር የለም፣ እግዚያብሄር ይረዳናል” ብለን ነው ተወስኖ የተገዛው::
ሲገዛም አቅም ኖሮን በቀላሉ አይደለም የተገዛው:: አቅም ስላልነበረን ባንክ የጠየቀንን ማሟላት አልቻልንም:: ተያዥ አምጡ ሲባል በወቅቱ የነበረው ኮሚቴ ብዙ ሰዎችን ጠይቋል:: አስር ሠዎች ፈቃደኛ ሆነን ፈርመናል:: እኔም በእግዚያብሄር ቸርነትና በረከት አንዱ ፈራሚ ነበርኩ:: ከማንም በላይ ገንዘን ሃብት ኖሮን ሳይሆን ፍቅራችንን እና በእግዚያብሄር ያለንን እምነት ለመግለጽ ነው የፈረምነው::
አስር ዓመት ነበር ውሉ:: እግዚያብሄር ይመስገን 10 አመትም ሳይሞላው እዳው ተከፍሎ አለቀ:: በእግዚያብሄር እምነት መጣል ፍሬውን እንዲህ ያሳያል:: በአገልግሎት አውቀን ሳይሆን እግዚያብሄር ፈቅዶ እጣ ፈንታው በረከቱ ደረሰን:: እግዚያብሄር በመራን ሞክረን ጥረን እዚህ ተደርሷል::
በመጨረሻም ማለት የምፈልገው ነገር የሃይማኖት አባቶችን አገልጋዮቻችንን እንደ አባት እንደ አያት እንድናያቸው ነው:: እንደ ቤተሰብ መደገፍ አለብን:: በሰው ሃገር እንደመኖራችን መረዳዳት መተሳሰብ ይገባናል ባይ ነኝ::
እግዚአብሔር ለሃገራችን ሰላም አውርዶ በፍቅር ይጎብኝልን:: እንዲሁም ያለንበትም ሃገር አሜሪካን ይጠብቅልን:: ስለሁሉም ነገር እግዚአብሄር ይመስገን::
ወ/ሮ ፈትለወርቅ ሃይለማርያም ብሩክ
ግሪክና ግብጾች ቤተክርስቲያን ለመገልገል ስንጠይቅ እኔም አንዷ ተሳታፊ ነበርኩ:: ሁሉም ደክሟል፤ ሁሉም የየራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል::
በዛ ግዜ የግብጽና የግሪክ ቤተክርስቲያን የሃበሻ ቤተክርስቲያን ነበር የሚመስለው:: አዳራሹን የምንሞላው እኛ ነበርን:: አማራጭ የለንማ የት እንሂድ? እኔና ቤተሰቤ ሮማንያ ቤተክርስቲያን ሁሉ እንሄድ ነበር::
እኔ እንደውም እድለኛ ነኝ:: በሃበሻ ቄስ ግሪክ ቸርች ነው የተዳርኩት:: ስነ ስርዓቱ ተጠብቆ ደስ የሚል ፕሮግራም ነበር::
የማርያምን መቋቋም እና እዚህ ደረጃ መድረስ ሳስበው ህልም ነው የሚመስለኝ:: ይህች ማርያም ተዓምረኛ ማርያም ናት:: እመቤቴ ማርያም አትለየን:: ክፉ አታሳየን፣ ትጠብቀን የዘወትር ጸሎቴ ነው::
ወ/ሮ ውብአደይ በቀለ
እዚህ ሃገር እንደመጣሁ 3 ዓመት ያህል ሃበሻ እንኳን አይቼ አላውቅም ነበር:: ሃበሾች ቤተክርስቲያን መሰባሰባቸውን የምሰራበት ቦታ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ተለጥፎ አንብቤ ነው የሄድኩት:: እግዚያብሄር ሊያሰባስበንም፣ ሊፈትነንም ሊሆን ይችላል በወቅቱ ብዙ ነገር ደርሶብናል::
እኔ እዚህ ሃገር ስመጣ የተቀበሉኝ ጴንጤዎች ናቸው:: ገና አዲስ ሆኜ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ነው ብለው ጴንጤ ቤተክርስቲያን ወስደውኝ ነበር:: ጽናጽል መቋሚያ ይዘዋል:: መዝሙር ዘመሩ:: በኋላ ሲነግሩኝ ተሃድሶ ነው አሉኝ በጣም ተበሳጨሁ:: ማርያም ስትቋቋም “በማን ስም ይሰየም?” የሚል ጥያቄ ሲመጣ እኔ ነኝ “ማርያም መሆን አለባት” ያልኩት:: “የማርያምን አማላጅነት የሚያምን ይከተለን፣ እናቱን ሳናስቀድም ሌሎችን ማስቀደም የለብንም” አልኩኝ::
በዛ ሰዓት ጠረጴዛ ልብስ ከቤት እየወሰድን፣ መስቀል በእጃችን በእንጨት እየሰራን ነበር የምንገለገለው:: ለአንድ እሁድ ግማሽ ቀን 700 $ ኪራይ እየከፈልን የተገለገልንበት ግዜ ነበር:: እቃውን ሁሉ በእኔ መኪና ጭኜ እቤት ወስጄ፣ በሳምንቱ እያመላለስኩ ነበር የምንገለገለው:: ለእቃ እና መዘምራን የሚለማመዱበት አንድ ክፍል ለቅቄ ነበር:: በዛ ሰዓት ልጆቼን ለማየት በየዓመቱ ሃገር ቤት እመላለስ ስለነበረ በመጣሁ ቁጥር ለቤተክርስቲያን አንድ እቃ ሳልይዝ አልመጣም ነበር:: በዛ ሰዓት የነበሩ የልጆች መማሪያ ፊደሎች ዛሬ ለማስታወሻ እንኳን አልቀሩም:: ተበታትነው ቀርተዋል::
ዛሬ እዚህ ደረጃ መደረሱ በጣም ትልቅ ነገር ነው:: ወደፊትም ትልቅ ደረጃ እንደምንደርስ ተስፋ አደርጋለሁ:: እዚህ ያደረሰን እግዚያብሄር ነገ የሚልክልንን ደግሞ በተስፋ እንጠብቃለን::
ቤተ ክርስቲያኑን ከመመስረት ጀምሮ ምዕመናን በማሰባሰብ ሌሎችም በዚህ ጽሁፍ ያልተካተቱ ባለውለታዎች እንዳሉ ለማስታወስ እንወዳለን:: ዛሬ የራሳችን የሆነ ንብረት አለን ለማለት ያስደፈረን የበርካቶች ተሳትፎ እንደተጠበቀ ሆኖ በማስተባበሩ በኩል ደግሞ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ያበረከቱ እህቶችና ወንድሞች አሉ:: አሁንም ከብዙዎች ጥቂቶቹን አነጋግረናል::
ወ/ት ጠጄ ኃይሉ
እኔ በበኩሌ የሰራሁት ስራ የለም:: ኮሚቴ ውስጥ በምሰራበት ወቅት ነው መሬት ለመግዛት የታሰበው:: በርግጥ የሚጠቅመን ቦታ ነው:: በዓል ብናከብር፣ ፓርኪንግ ብንፈልግ ይጠቅመናል የሚል ሃሳብ ነበር:: እኔም ይጠቅማል ተብሎ ከተገዛ ፈንድ ሬይዝ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብዬ ቃል ገባሁ::
በርግጥ ገንዘብ ያዥ ሆኜ እንዳየሁት ወርሃዊ መዋጮ እንኳ ለማዋጣት ጎበዝ አይደለንም:: በርግጥ እግዚያብሄር ከፈቀደ ይከፈላል ብዬ ነበር የማምነው:: እኔ በህይወቴ ሰው ከፈለገ እና ከጣረ የማይቻል ነገር አለ ብዬ አላስብም:: ሰው ከተባበረ የማይቻል ነገር የለም:: ይቻላል!!! ነበር የኔ አቋም::
የዛሬ 2 ዓመት ነበር የተገዛው:: ወቅቱ ሰው ቤት በብዛት የገዛበት፣ ኢኮኖሚው የወደቀበት እንዲሁም ብዙ ሰው ስራ አጥ የነበረበት ወቅት ነበር:: በመጀመሪያው ዙር መክፈል የሚጠበቅብን 100 ሺ ዶላር ነበር:: ያን ያህል ተዋጥቶ ይከፈላል ብለን አላሰብንም:: የተወሰነ ቃል ከተገባ በብድር ሸፍነን ቃል የተገባው ሲመጣ ብድሩ ይከፈላል የሚል ሃሳብ ይዘን ነበር የተነሳነው::
ገና ስራውን ስጀምር እግዜር እንዲረዳን ጸሎት ጀመርኩ:: ጠዋት እና ማታ ነበር ጸሎት የማደርገው:: መጀመሪያ አባን ነው ያማከርኳቸው:: እሳቸው የእግዚያብሄር ሰው ስለሆኑ እግዜር መንገዱን ያመላክታቸዋል:: በጣም ነው የተባበሩን::
በሚገርም ሁኔታ ገንዘቡ ከተጠበቀው በላይ ተዋጣ:: ህዝቡ በሚገርም ሁኔታ ተባበረ:: የጎደለው በብድር ተሟልቶ መሬቱ 100 ሺ ዶላሩ ተከፍሎ ተገዛ:: ቃል የተገባው ገንዘብ ሲመጣ ከግለሰብ የተበደርነውን እዳችንን ከፈልን::
እዳችንን 80 ሺውን በሁለት ዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ይጠበቅብን ነበር:: በወቅቱ ለአጥር ማሰሪያ፣ ኤሲ ሲበላሽ ስናስጠግን፣ ሌቦች ገብተው ሰርቀውን ነበር እሱን ለማሰራት በጣም ብዙ ወጪ ነበረብን:: በእነዚህ ወጪዎች ምክንያት 80 ሺውን መክፈል አልቻልንም:: ባለፈው አመት ፌብሩዋሪ ላይ ተከፍሎ ማለቅ ነበረበት::
አሁንም አባን አማከርኳቸው:: “ሌላ ቤተ ክርስቲያን እኮ ሰው ተከፋፍሎ እዳ ይከፍላል” ነበር ያሉት አባ:: በርግጥ የመጀመሪያው ግዜ እንደዛ ብለው ወጥተው ተናግረው ነው ያ ሁሉ ገንዘን ተዋጥቶ የተከፈለው:: አሁን ግን እንደ በፊቱ ማለት አልቻሉም እኔ ወጥቼ ለህዝቡ ተናገርኩ:: የዛን እለት እግዚያብሄር በሚያውቀው የቅዳሴ ስርዓቱን እንኳ በስርዓት አልተከታተልኩም:: ከእግዚያብሄር ጋ ስነጋገር ስጸልይ ነው የቆየሁት::
የመክፈያ ግዜያችን ሳይደርስ ዕዳችንን ለመክፈል ያልተደረገ ነገር አልነበረም:: ፈንድ ሬይዝ ተደረገ፣ ዕቃ ጨረታ ወጣ፣ ስዕሎች ተሸጡ፣ ሰው ቃል ገባ…. ብዙ ብዙ ተለፍቶ ከታሰበው በላይ ገብቶ እዳችንን በወቅቱ ከፈልን:: እንደውም የአዲሱን መሬት ብቻ ሳይሆን የቤቱን የቀረውን እዳ ሁሉ አጠናቀቅን::
እኔ በበኩሌ ትልቅ ኃላፊነት ነበር የተሸከምኩት:: በህይወቴ እግዚያብሄርን እንደዛ የተማጸንኩበት ወቅት አልነበረም:: ስቀመጥ ስነሳ ስለ ዕዳችን ነበር የማስበው:: ሎቶሪ ለእኔ ወይ ለአንድ ሰው በደረሰን እና እዳችንን በከፈልን ብዬ ሁሉ ተመኝቻለሁ:: በወቅቱ ካልተከፈለ በቀን 100 ዶላር በወር 3 ሺ ዶላር ተጨማሪ እዳ ይሆንብን ነበር:: በርግጥ በወቅቱ ባይከፈል ኖሮ ያንን ቦታ እናጣ ነበር ማለት ይቻላል::
በየሰው ቤት እየደወልኩ ነበር ሰውን ያስቸገርኩት:: አባል ያልሆኑ ሰዎች ሁሉ ረድተውናል:: ዶክተር ሰለሞን ለምሳሌ መመስገን አለበት:: መጀመሪያ 5 ሺ በሁለተኛ ዙር 2 ሺ ዶላር ነው የሰጠን:: ህዝቡ በጠቅላላ ሊመሰገን ይገባዋል:: ከአቅሙ በላይ ነው ያበረከተው ማለት እችላለሁ::
ዛሬ ውጡ ሰዓት ደረሰ ወይም ልጆቻችሁ ረበሹ አንባልም:: አባራሪም የለብንም:: እግዚያብሄር ይመስገን የራሳችን ንብረት ባለቤቶች ሆነናል:: ይህ ቤት ሳይገዛ ብዙ ቦታ ተንከራተናል:: ያ ሁሉ ችግር ያሳለፈ ህዝብ ዛሬ ይህን ሲመለከት ለእግዚያብሄር ምን ይሳነዋል ከማለት ውጪ ምን ይባላል?
ወደፊት ደግሞ ከራሳችን በፊት የእግዚያብሄርን ቤት አስቀድመን፣ ከወርም ሆነ ከአመት ገቢያችን ላይ የሚገባንን አስራት ከፍለን፤ ይህችን ቤተክርስቲያን ትልቅ ደረጃ እናደርሳታለን ብዬ አምናለሁ:: እኔ ስራ ቦታ ያለኝን ገጠመኝ መናገር እፈልጋለሁ:: አንድ ጓደኛዬ በአንድ ወቅት ለእኔ መክፈል የነበረባት ገንዘን ነበር:: እናም ቼክ ልትጽፍልኝ ጀመረችና “ቆይ ቆይ መጀመሪያ ሌላ መጻፍ ያለብኝ ቼክ አለ” ብላ መጻፍ ጀመረች:: “ደግሞ ይሄ ለማን ነው?” ብዬ ጠየኳት:: “የቤተክርስቲያን አስራት ነው:: በቼክ ከማገኘው ገቢ 10 % ካልሰጠሁ ወር መድረስ አልችልም:: ቢሌን እንኳ ከፍዬ ሳልጨርስ ብሩ ያልቅብኛል” አለችኝ:: እነሱ ምን ያህል ተጠንቅቀው አስራታቸውን እንደሚከፍሉ ሳስብ ይገርመኛል:: እኛ ግን በዚህ በኩል ብዙ ይቀረናል:: እንኳን ከምናገነው 10 % ሂሳብ ሰርተን ልንከፍል በወር የምንከፍላትን 30 $ እንኳ አስበው የሚከፍሉ በጣም ጥቂቶች ናቸው:: በርግጥ አስራት በኩራት ላይ ጠንክረን ለእግዚያብሄር የሚገባውን ለእግዚያብሄር ብንሰጥ ያለን መሬት ላይ ትልቅ ቤት መስራት እንችላለን:: የሃይማኖትና የመጽሃፍ ቅዱስ ጥናትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስባለሁ::
አቶ አምሳሉ በላይ
እኔ በ1993 እዚህ ሃገር ስመጣ ጥቂት ሰዎች ተሰባስበው ስለ ቤተክርስትያን ይነጋገሩ ነበር:: ጋሽ አርአያ ሽፈራው ቤቱ እያሰባሰበ ቤተክርስቲያን ስለመመስረት ያነጋግረን ነበር:: በዚህ አጋጣሚ መመስገን ያለበት ሰው ነው:: የተወሰነ ግዜ እንገናኝ ነበር:: በኋላ አቅም ስናጣ የዚህ ሃገር ሩጫ ሲያባክነን ተጠፋፋን:: ከ 3 እና 4 አመት በኋላ እንቅስቃሴ ሲጀመር እንደገና ተሰባሰብን::
ይህ ስብስብ ነው ዛሬ ለቆመው ቤተክርስቲያን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው:: የዚህን አገር ኑሮ እናውቀዋለን:: በሩጫና በድካም የተሞላ ነው:: ይህ ቤተክርስቲያን መኖሩ በጋራ ተሰባስበን እግዚያብሄርን እንድናመልክ፣ የደከም ህይወታችንን አረፍ የምናደርግበት ቦታ እንዲኖረን አድርጎናል::ይህ ቤተክርስቲያን የእምነት ቦታ ብቻ አይደለም:: እምነታችንን ቤታችንም ሆነን ልናመልክ እንችላለን:: ከምንም በላይ እግዚያብሄር ውስጣችንን መርምሮ ያውቃል:: ከእምነታችን ጎን ለጎን ፍቅርን የምናገኝበት፣ ኑሯችንን ህይወታችንን የምንጫወትበት፣ ሃዘን ደስታችንን የሚካፈለንን የራሳችንን ማህበረሰብ የምናገኝበት ቦታ ነው:: ልጆቻችን ራሳቸው ብዙ ነገር ይማራሉ:: ራሳቸውን የሚመስል ጓደኛ ያገኙበታል:: ጨዋታውን ይወዱታል:: ሳምንት እሁድ እስኪደርስ ይናፍቃቸዋል:: ሳንችል እንኳ ብንቀር ሰላም የላቸውም:: እንደምንም ብለን እንድንሄድ ያስገድዱናል::
ለዚህ ህዝብ እጅግ አስፈላጊ ቦታ ቢኖር ቤተክርስቲያን ነው:: እኔ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ነው የምለው:: አንደኛ እግዚያብሄርን አመልክበታለሁ፣ ሁለተኛ ድካሜን የምወጣበት እህት ወንድሞቼን የማገኝበት ቤቴ ነው:: እኔ ከ2008 እስከ 2011 መጨረሻ ድረስ በቦርድ ሊቀመንበርነት አገልግያለሁ:: የእኛ ስራ ለህዝቡ ያለውን ነገር ማሳወቅ፣ የሚያስፈልገውን ነገር መጠየቅ ነው:: ይህች ቤተክርስቲያን ያላት ሃብት ህዝብ ነው:: ሌላ የገቢ ምንጭ የላትም:: ቤተክርስቲያኗ ህዝቧን እንደምታገለግል ሁሉ ህዝቡም የሚጠበቅበትን በማድረግ ግዴታውን ከሞላ ጎደል እየተወጣ ነው ለማለት እደፍራለሁ::
እዳችንን ለመክፈል በተንቀሳቀስንበት ወቅት ህዝቡ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ፣ ጊዜውን በመስጠት እንዲሁም በሃሳብ ረድቶናል:: ያን ያህል ገንዘብ በዛች በአጭር ግዜ ተሰብስቦ እንዴት ተከፈለ? ሳስበው ራሱ ይገርመኛል:: የእግዚያብሄር ተአምር ነው እንጂ ምንም ሊባል አይችልም::
በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው ነገር የዚህችን ቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ደንብ ያወጡ ሰዎች ሁሌም መመስገን አለባቸው:: በጣም ረቂቅና ችግር ፈቺ ህገ ደንብ ነው ያለን:: በተለያዩ ሃገራት የምንሰማውና የምናየው ሽኩቻ፣ ሰላም ማጣት እዚህ የለም:: በተወሰነ ወቅት የተነሳውን ችግርም መተዳደሪያ ደንቡን በመከተል ብቻ ፈተነዋል ማለት እችላለሁ:: ለብሄር እና ለፖለቲካ ቦታ አለመስጠታችን፣ ህዝቡን በፍቅር አስተሳስሮ እዚህ ደረጃ አድርሶታል:: ወደፊትም ከዚህ የበለጠ ትልቅ ደረጃ እንደምንደርስ አምናለሁ::